ኢትዮጵያ በወንጀል የምትፈልጋቸውን ሰዎች አሜሪካ አሳልፋ እንድትሰጣት ጥያቄ አቅርባለች፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአሜሪካው ኤፍ.ቢ.አይ (FBI) ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አምባሳደሩ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ኮሚሽነሩ በውይያታቸው ወቅት ጠይቀዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በአሜሪካን ሀገር እየኖሩ የሀገሪቱን ሰላም እያወኩ ነው በሚል የምትጠረጥራቸውን ሰዎች ተላልፈው እንዲሰጧት ለአምባሳደሩ ጥያቄ እንዳቀረቡም ተገልጿል፡፡
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በአሜሪካን መንግሥት የሚፈለጉ ወንጀለኞችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ተብሏል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተመሳሳይ ድጋፎችን እንድታደርግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ሲል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ወንጀሎችን አሳልፉ መስጠት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ በርካታ ወንጀለኞችን አሳልፋ ሰጥታለች፡፡
በተለይም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወንጀል ሰርተው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሚደበቁ ሲሆን በዚህ ስምምነት መሰረት ተጠርጣሪዎቹ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡
ለአብነትም ከአምስት ዓመት በፊት ዮሐንስ ነሲቡ የተባለ ትውልደ ኢተዮጵያዊ ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጥ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወሰነው መሰረት ሚያዚያ 2019 ላይ ለአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ባልደረቦች ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡
ግለሰቡ በአሜሪካን አገር በቨርጂኒያ ግዛት ኹለት የኢትዮጵያ የዘር ሃረግ ያላቸውን ሔኖክ ዩሐንስን እና ቅድስት ሰሜነህ የተባሉ ኢትዮጵያ አሜሪካዊያንን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከሁለት ዓመት በኋላ ለአሜሪካው የምርመራ ቢሮ ተላልፎ መሰጠቱ አይዘነጋም፡፡
በአንጻሩ ኢትዮጵያ እንደ ታዋቂው ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው፣ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እና ሌሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አስተያየት በሚሰጡ ፖለቲከኞች እና አንቂዎች ላይ የእስር ማዘዣ እና ክስ የመሰረተች ሲሆን እነዚህ ተጠርጣሪዎች በአሜሪካ ተላልፈው እንዲሰጧት ትፈልጋለች፡፡
ይሁንና አሜሪካ በኢትዮጵያ ጥያቄ መሰረት በፖለቲካ ምክንያት ክስ የተመሰረተባቸውን እና በሀገሯ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን አሳልፋ ስለመስጠቷ እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም፡፡