የኢትዮጵያ መንግስት ምዕራባውያን በፕሬስ ነጻነት አያያዝ ዙሪያ ያቀረቡበትን ትችት እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ 18 ምዕራባውያን ሀገራት ኢምቢሲዎች ‘የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን’ አስመልክተው ባወጡት የጋራ መግለጫ የኢትዮጵያን የጋዜጠኞች አያያዝ ተችተዋል።
በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር ከጠየቁ ሀገራት መካከልም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ ቤልጂየም፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ኔዘርላንድ እና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡
ሀገራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ስራቸውን በመስራታቸው “ማስፈራሪያ እና እስር ይደርሰባቸዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ሀገራቱ በኢምባሲዎቻቸው በኩል ያወጡትን መግለጫ እንደማይቀበለው ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከሁሉም አጋሮቿ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ገንቢ የሆነ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የገለጸው ሚኒስቴሩ “አባታዊ ወደሆነ መግለጫ ማምራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚጎዳ እና የህግ የበላይነት የሚሸረሽር” ነው ብሏል።
ኢምባሲዎቹ ካሉበት ሀገር በእንዲህ አይነት መልኩ ግንኙነት ማካሄድ ተገቢነት የለውም ሲል ገልጿል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሲፒጄ እና ሂማን ራይትስዎችን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለአግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞች መኖራቸውን በመግለጽ ባለስልጣናት እንዲለቋቸው በተለያየ ጊዜ ጠይቀዋል።
የጋዜጠኞቾ መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ ከወራት በፊት ባወጣው አመታዋ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ስምንት ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ውስጥ ሁለተኛ የጋዜጠኞች አሳሪ አድርጓታል።
እንደ ሲፒጄ ሪፖርት ከሆነ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን እንግልት በመፍራት ከሙያው እና ከሀገር እየራቁ ይገኛሉ፡፡
ተቋሙ አክሎም ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ አባይ ዘውዱ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ቴዎድሮስ ዘርፉ፣ መስከረም አበራ፣በቃሉ አላምረው እና ሌሎችም ለእስር ተዳርገዋል ያለ ሲሆን መንግስት ጋዜጠኞቹን ከእስር እንዲለቅም ጠይቋል፡፡