በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ አምስት በመቶ ያህሉ ሲጋራ አጫሾች እንደሆኑ አንድ ጥናት አመላከተ፡፡
በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከአጫሾች በሚወጣ የትምባሆ ጭስ እንደሚቸገሩ ከዚህ በፊት የተደረገ ጥናት ያሳያል፡፡
ጥናቱ ኢትዮጵያ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ ስኬታማ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነችም ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ እና የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በየጊዜው ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡
ከእነዚህ መካከልም ትምባሆ መግዛት የሚችሉት እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የመዝናኛ እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ትምባሆ ማጨስ እንደማይቻል፣ ሰው በተሰበሰበባቸው ቦታው ትምባሆ ማጨስ እና መስጨስ መከልከሉ አስገዳጅ ህግ መደረጋቸው ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ህጻናትን ከትንባሆ ነጻ የማደረግ እንቅስቃሴ (Campaign for Tobacco Free Kids ) ኢትዮጵያ ያለባትን የትንባሆ አምራቾች እና ተጠቃሚዎች ግፊትን ተቋቁማ ለውጥ አምጪ የትንባሆ ቁጥጥር አዋጆች ማጽደቋን አድንቋል፡፡
የዚህ ዓለም አቀፍ ጤና ተቋም የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬከተር ቢንቶው ካማራ እንዳሉት የትንባሆ ቁጥጥሩ ውጤታማነት መሰረት ያደረገው የተለያዩ መንገስታዊ ተቋማት በህብረት ከመስራታቸው ባለፈ እንደ ሀገር የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት 2023 ሪፖርት ከሆነ በዓለም ላይ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ ሲጋራ የሚያጨስ ሲሆን በየዓመቱ 8 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በሲጋራ ማጨስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
ሲጋራ ማጨስ በተለይም ለልብ ህመም፣ ሳምባ ካንሰር፣ ስኳር፣ ለስትሮክ እና ሌሎች ጽኑ ህመሞች የሚዳርግ ሲሆን በ2023 ዓመት ብቻ ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸው አጥተዋል፡፡