በአዲስ አበባ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ ከ6 ሺህ በላይ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶች መታሸጋቸው ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ባለፉት 9 ወራት የህብረተሰቡን ሰላም አውከዋል ባላቸው የተለያዩ ስራዎች ላይ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል፡፡
የቢሮው ሀላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ የውርርድ ቤቶችን ጨምሮ ጫት ማስቃም፣ ሽሻ ማስጨስና የመሳሰሉ ጉዳዮች ይፈፀሙባቸው የነበሩና የወንጀል ድርጊት የሚታይባቸው ተግባራት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ድርጊቶች ትምህርት ቤቶች አካባቢ የመማር ማስተማር ሂደትን እያስተጓጉሉ የነበሩ ናቸውም ተብሏል።
የከተማዋ አስተዳድር ከዘጋቸው ተቋማት መካከል 6 ሺህ 726 የሚሆኑ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶች መታሸጋቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ የንግድ ድርጅቶች ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ እንዲቀይሩ እየተደረገ መሆኑን ሃላፊዋ አክለው ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤት ቅጣት ጥሎባቸው ከታሸገ በኋላ እቃውን እንዲያወጡ ተጠይቀው ፍቃደኛ ባልሆኑት ላይ ፖሊስና የደንብ ማስከበር አካላት ከሰላምና ጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ህግን ለማስከበር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የከተማው አስተዳድር ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ከ3 ሺህ በላይ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶችን ዘግቶ ነበር፡፡
አስተዳድሩ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶችን የዘጋው እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸው እና ሌሎች ህጎችን ጥሰዋል በሚል ምክንት ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ50 በላይ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶች ወደ ስራ የገቡ ቢሆንም ድርጅቶቹ ወጣቶችን ወደ ቁማር እና ሱስ እያስገቡ ነው የሚሉ አስተያየቶች ሲቀርብባቸው ቆይቷል፡፡
የሴቶች፣ ወጣቶች እና ህጸናት ጉዳዮች ሚኒስቴር በበኩሉ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶች በኢትዮጵያ ሊፈቀድ እንደማይገባ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡
የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶች በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ቀውስ እንዲፈጠር፣ ትዳር እንዲፈርስ እና ሌሎች ሰዎችን ሊጎዱ የሚችሉ ጉዳቶችን እያስከተለ በመሆኑ እንዲከለከል ሲጠይቅም ቆይቷል፡፡
የስፖርታዊ ውርርድ ድርጅቶች ማህበር በበኩሉ እኛ ህጉ በሚፈቅድልን መሰረት ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር የንግድ ፈቃድ አውጥተን እየሰራን እንጂ ህገወጥ ስራ አልሰራንም ሲል አስታውቋል፡፡
መንግስት የስፖርታዊ ውርርድ ድርጅቶችን በጅምላ መዝጋቱ አግባብ አለመሆኑን የገለጸው ማህበሩ ከተፈቀደላቸው አሰራር እና ንግድ ፈቃድ ውጪ እንዲሁም ህጉን አክብረው የማይሰሩትን ነጥሎ እንዲቀጣም ጠይቋል፡፡
ማህበሩ አክሎም ኢትዮጵያ ከህጋዊ የስፖርታዊ ውርርድ ቤቶች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ በግብር መልክ እያገኘች እንደሆነም አስታውቋል፡፡