የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያዊያን የቪዛ መጠየቂያ ጊዜን ከ15 ቀናት ወደ 45 ቀናት ከፍ አድርጓል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ቪዛ የመስጠትን ሂደት ላይ ጊዜያው ገደቦችን ማስቀመጡን አስታውቋል።
ህብረቱ በሳለፈው ውሳኔ የህብረቱ ለአባል ሃገራት ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን ቪዛ አመልካቾች ቪዛ ሲፈልጉ ሊያሟሉ ይገባቸዋል ያላቸውን መስፈርቶችም አስቀምጧል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን የአውሮፓ ሀገራት ቪዛን ለማግኘት አስፈላጊ ሰነዶችን እንዲያቀርቡ እና በአውሮፓ ህብረት ህግ የተቀመጠውን መደበኛ መስፈርቶች እንዲያሟሉ ይገደዳሉ ተብሏል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከሁለት ጊዜ በላይ ወደ አውሮፓ ሀገራት ለመግባት የሚያስችለውን ቪዛ ለኢትዮጵያውያን መስጠት አይችሉም ሲልም ከልክሏል።
ለዲፕሎማቲክ እና ለአገልግሎት ፓስፖርቶች የቪዛ ክፍያን በተመለከተም ኢትዮጵያውያን ቪዛ ሲፈልጉ መደበኛውን የቪዛ ክፍያ ለመክፈል ይገደዳሉ ብሏል ህብረቱ።
መደበኛው ቪዛ ለማግኘት የሚጠበቀው የ15 ቀን ጊዜ ወደ 45 ቀን መራዘሙንም የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በመግለጫው አመላክቷል።
የቪዛ ገደቡ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እንዲተላለፍ ምክንያት የሆነውም ህብረቱ “ከኢትዮጵያ መንግስት በቂ ትብብር እያገኘሁ አይደለም” በሚል ነው።
የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያ በህገ-ወጥ መንገድ በአውሮፓ ህብረት የሚቆዩ ዜጎቿን በማስመለስ ረገድ የምታደርገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ የቪዛ ገደብ ውሳኔውን ማሳለፉንም አስታውቋል
ይሁንና የአውሮፓ ህብረት አዲስ የቪዛ ገደብ ውሳኔ ለምን ያክል ግዜ እንደሚቆይ አልጠቀሰም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በአውሮፓ ህብረት አዲስ ገደብ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ከሚያደርጉ አጋሮች መካከል ዋነኛው ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ የ30 በመቶ ድርሻ አለው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለትምህርት ስኮላርሽፕ እድል ወደ አውሮፓ ሀገራት ዩንቨርሲቲዎች በብዛት ከሚቀኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ዋነኞቹም ናቸው፡፡
የአውሮፓ ህብረት በተለይም በኢትዮጵያ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያሳስቡት በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያክልሎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ንጹሃን ግድያዎች እንዲቆሙ፣ ንጹሃን ከጥቃት እንዲጠበቁ እና በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳም ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርቧል፡፡