የአፍሪካ ህብረት በራያ እና አላማጣ የተከሰተው አዲስ ግጭት እንደሚያሳስበው ገለጸ

የአማራ እና የትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አላማጣ እና አካባቢዋ ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት መግለጫ አውጥቷል።

መግለጫው የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት በአወዛጋቢዎቹ ራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፎላ “በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ያሉ ውጥረቶችን” በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጿል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተደረሰው የፌደራል መንግስት እና የህወሓት የዘላቂ ሰላም ስምምነት፣ ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው “አወዛጋቢ ቦታዎች” በህገመንግስቱ መሰረት እልባት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ይጠቅሳል።

ሊቀመንበሩ ሁለቱም ወገኖች ግጭት ከማባባስ እንዲታቀቡ እና የአካባቢውን ንጹሃን መፈናቀል እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የሰባት ሀገራት ኤምባሲዎች በአማራ እና ትግራይ ከልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ያጋጠመው አዲስ ግጭት እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ እና አማራ ክልል መካከል “አጨቃጫቂ ቦታዎች” ሲሉ በገለጿቸው አከባቢዎች የተፈጠረው ውጥረት አስግቶናል ሲሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ሁሉም አካላት ትጥቅ የማስፈታት፣ ተዋጊዎችን የመበተን እና መልሶ የማቋቋም እንዲሁም ተፈናቃዮችን በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀያቸው የመመለስ  ጥረት እንዲያፋጥኑ ኢምባሲዎቹ ጠይቀዋል።

እንዲሁም ሁኔታዎች እንዲረጋጉ እና ንጹሃንን ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የጠየቁት ኢምባሲዎቹ በኢትዮጵያ የሚታየው ውስብስብ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውስ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው እና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው ሁሉን አቀፍ ንግግር በባለድርሻ አካላት መካከል ሲደረግ ብቻ ነው ሲሉም አሳስበዋል።

የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የጠየቁት ሊቀመንበሩ ለአወዛጋቢ ቦታዎች መፍትሄ ይሰጣል ያሉት የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የፌዴራል መንግስት የራያ አካቢዎችን ጨምሮ በሌሎች አወዛጋቢ አካባቢዎች የፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይል እንደሚሰማራ እና አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ወደፈለጉበት እንዲካለሉ እንደሚደረግ ገልጾ ነበር።

ይሁን እንጂ መንግስታዊ መዋቅር ዘርግቶ የራያ አላማጣ እና አካባቢዎቹን እያስተዳዳረ የነበረው የአማራ ክልል መንግስት፣ ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሶ ለአራተኛ ዙር ወረራ እንደከፈተበት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ከሶ ነበር።

የክልሉ መንግስት በዚህ መግለጫው፣ ህወሓት ወደ ግጭት እንዳይገባ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ጥረት ቢያደርግም፣ ካለፉት ጦርነት አልተማረም ያለው ህወሓት ጦርነት እንደከፈተበት ገልጿል።

ህወሓት ወሯቸዋል ካላቸው የራያ አካባቢዎችም እንዲወጣም የአማራ ክልል በመግጫው ጠይቋል።

የተመድ የሰብአዊ መብት ቢሮ እንደገጸው በእነዚህ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎች ከ50ሺ አልፏል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ደቡብ ትግራይ በሚለው ዞን ውስጥ ባሉ አወዛጋቢ ቦታዎች እየሆኑ ያሉ አዳዲስ ሁነቶች በስምምነቱ መሰረት የተደረጉ ናቸው ይላል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው የአማራ ክልል ካወጣው መግለጫ ቀደም ሲል በትዊተር ገጻቸው በራያ እና በሌሎቹ አወዛጋቢ አካባቢዎች ያሉት ሁነቶች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እየተፈጸሙ ያሉ ናቸው፤ ከአማራ ክልልም ይሁን ከፌደራል መንግስት ጋር ግጭት ማለታቸው ይታወሳል።

ህወሓት ስምምነት ጥሶ ወረራ ፈጽሞብኛል ስለሚለው የአማራ ክልል መንግስት መግለጫም ይሁን ሁነቶች በስምምነቱ መሰረት እየተካሄዱ ናቸው ስለሚለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስተያየት የፌደራል መንግስት ያለው የለም።

ስምምነትቱን ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲወቅሱ እንደነበር ይታወሳል።

ለሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አንድ ሊዮን ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ 29 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት ደግሞ መውደሙን የፌደራል መንግስት ገልጿል፡፡

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የተደረገው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ጦርነቱ የቆመ ቢሆንም ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገባ ስጋት ደቅኗል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *