ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አመታት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን እንድታዘጋጅ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ዋንጫን እ.ኤ.አ በ2029 ወይም በ2031 ለማዘጋጀት እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለእቅዱ መሳካትም ቢያንስ ስድስት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ካፍ ከዚህ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ መስፈርቶችን በማስቀመጡ ኢትዮጵያ አንድም ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም እንዳይኖራት አድርጓል ሲሉም አቶ ቀጀላ መርዳሳ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የካፍን ደረጃ የሚመጥኑ ስታዲየሞች የሌላት በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዘም ላሉ ጊዜያት ከሀገሩ ዉጪ ለመጫወት ተገድዶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።
የዉድድሩ አዘጋጅ ሀገራት ቢያንስ ስድስት ስታዲየሞችን እንዲያዘጋጁ ካፍ ቢያዝም ኢትዮጵያ እስካሁን የካፍን ደረጃ ያሟላ ስታዲየም የሌላት ሲሆን ውድድሩን ለማዘጋጀት እያደረገች ስላለው ዝግጅት የተባለ ነገር የለም፡፡
ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች አንድ ስታዲየም ያላት ቢህንም ከዚህ ውስጥ አንዱም የካፍን ደረጃ የማያሟላ ሲሆን በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው እና 62 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ አልቻለም፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም እስካሁን ዋንጫውን አንድ ጊዜ ብቻ ማሸነፍ ችላለች፡፡
በ1962 የአፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀችው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ተጫውታ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችላለች፡፡
በ1968 በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃን ይዛ እንዳጠናቀቀች ይታወቃል፡፡
ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረጉ የአግር ኳስ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያልቻለችው ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ዳግም በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው ውድድር ላይ መሳተፍ ችላለች፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈች ሲሆን አንድ ጊዜ ዋንጫ እንዲሁም አንድ ጊዜ ደግሞ አራተኛ ሆና ከማጠናቀቅ ባለፈ በቀሪዎቹ ውድድሮች ላይ ከምድቧ ማለፍ ሳትችል ቀርታለች፡፡
ግብጽ የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ካሜሩን አምስት ጊዜ ጋና አራት ጊዝ እንዲሁም ናይጀሪያ እና ኮቲዲቯር ደግሞ ሶስት ጊዜ አሸንፈዋል፡፡
በተወዳጁ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሀገራት ተጫዋቾች በርከት ያሉ ግቦችን በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አግቢነት ዝርዝር ውስጥ መካተት ችለዋል።
የካሜሮኑ ሳሙዔል ኤቶ ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን በ18 ግቦች የሚመራ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው መንግስቱ መንግስቱ ወርቁ 10 ጎሎች፣ የካሜሮን፣ የአይቮሪ ኮስት እና የግብጽ ተጫዋቾች በከፍተኛ የግብ አግቢነት ዝርዝሩ ተካተዋል።