በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3 ሺህ በላይ ህጻናት ከከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ጋር እንደሚወለዱ ተገለጸ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ላጋጠማቸው ህጻናት ድጋፍ በማድረግ ዘርፍ የተሰማራው “ስማይል ትሬን” የተሰኘው ተቋም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ መስራት ከጀመረ ከ20 በላይ ሆኖታል።

ድርጅቱ ከሌላኛው ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም ላይፍ ቦክስ ከተሰኘው ተቋም ጋር በመቀናጀት ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

እነዚህ ሁለት ተቋማት ቲም ክሌፍት ከተሰኘ የሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመቀናጀት የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ያጋጠማቸው ህጻናትን የቀዶ ጥገና ህክምና ለሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል።

ዶ/ር ቤቴል ሙልጌታ የስማይል ትሬን ምስራቅ አፍሪካ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ እርሳቸው የሚመሩት ቢሮ በኢትዮጵያ ካሉ ከ20 በላይ የግል እና የመንግስት ሆስፒታሎች ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ቤቴል ገለጻ ስማይል ትሬን በዓለም አቀፍ ደረጃ የከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ላጋጠማቸው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህጻናት የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ ደግሞ ከ37 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ላጋጠማቸው ህጻናት የነጻ ህክምና መስጠቱንም ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሆስፒታሎች ለቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የቀዶ ጥገና ህክምና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት ስራ በመስራት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

እንደ ዶክተር ቤቴል ገለጻ የከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ቀዶ ህክምናው ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ነው።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ የከንፈር ስንጥቃት ያጋጠማቸው ህጻናት በ3 ወር ውስጥ እንዲሁም ከላንቃ ስንጥቃት ጋር የተወለዱት ደግሞ በ9 ወር ውስጥ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል።

እንደ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ከሆነ የላንቃ ስንጥቃት ከሚያጋጥማቸው ህጻናት ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ህክምና ሳያገኙ ህይወታቸው ያልፋል።

የላንቃ ስንጥቃት የሚያጋጥማቸው ህጻናት ህክምና ካልተደረገለት የንግግር እና አመጋገብ ችግር ስለሚፈጥርባቸው ህይወታቸው ያልፋልም ተብላል።

ስማይል ትሬን ከላይፍ ቦክስ ጋር በመተባበር ቲም ክሌፍት ከተሰኘ ተቋም ጋር ለቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ሲወስዱ ያገኘናቸው አባይነሽ መንግስቴ አንዷ ናቸው።

አባይነሽ መንግስቴ በአዲስ አበባ በሚገኘው ኪዩር ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ባልደረባ ሲሆኑ የማደንዘዣ ህክምና ባለሙያም ናቸው።

ሆስፒታሉ ከሚሰጣቸው የቀዶ ህክምና አገልግሎቶች መካከል አንዱ የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ያጋጠማቸውን ህጻናት ህክምና እየሰጠ መሆኑን አባይነሽ ነግረውናል።

እንዲህ አይነት ችግር ያጋጠማቸው ህጻናት በሪፈር እና እንደ ስማይል ትሬን አይነት አጋር ተቋማት በኩል ወደ ኪዩር ሆስፒታል እየመጡ ህክምናው በነጻ እየተሰጣቸው እንደሆነም አክለዋል።

የከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ቀዶ ጥገና ህክምና ተያያዥ ድጋፎችን እና ልዩ ትኩረቶችን የሚፈልግ በመሆኑ በቡድን መስራትን ይጠይቃልም ብለዋል።

በተለይም ይህ ችግር ያጋጠማቸው ህጻናት የክብደት መቀነስ፣ የስነ ልቦና ችግሮች፣ መገለል እና የንግግር ችግሮች ስላሉ ቀዶ ጥገናውን በማድረግ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ አጠቃላይ በዚህ ህክምና ውስጥ ያሉ ተያያዥ ችግሮችን ማወቅ እንደሚጠይቅም አባይነሽ ጠቅሰዋል።

ዶክተር ይገረሙ ከበደ በአለርት ሆስፒታል የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ሲሆኑ ላለፉት 20 ዓመታት እና ከዛ በላይ በዚሁ ቀዶ ህክምና ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር ባለው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ነግረውናል።

ከከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ጋር እሚወለዱ ህጻናት መገለል ያጋጥማቸዋል ያሉት ዶክተር ይገረሙ ወላጆችም እንዲህ አይነት ልጅ ሲወልዱ ከፈጣሪ ቁጣ ጋር በማገናኘት ራሳቸውንም ህጻናቱንም ለከፋ ችግር እንደሚዳርጉ ተናግረዋል።

ችግሩ የአመለካከት በመሆኑ ምክንያት የላንቃ እና ከንፈር ስንጥቃት በህክምና እንደሚድን የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት ይገባልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ከከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ጋር በተያያዘ የሚወለዱ ህጻናት በህክምና የሚድን የማይመስላቸው ሰዎች በመኖራቸው ወደ ህክምና ተቋማት በቶሎ አያመጧቸውም። ዘግይተው ሲሙጡ ደግሞ በህክምናው ውጤታማነት ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ዶክተር ይገረሙ ጠቅሰዋል።

በዓለም ላይ የ3 ደቂቃ አንድ ህጻን በከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት ጋር ሲወለድ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እያገኙ ያሉ ህጻናት ቁጥር ደግሞ  በአምስት ደቂቃ አንድ ብቻ በመሆኑ የበለጠ መስራት ይጠይቃልም ብለዋል።

የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ምክንያት ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “የችግሩ ትክክለኛ መነሻ እስካሁን ባይታወቅም አፍሪካ እና እስያ ላይ በስፋት አለ። ነገር ግን መነሻ ይሆናሉ ተብሎ የሚገመቱት በእናቶች አመጋገብ በተለይም በእርግዝና ወቅት በቂ የፎሊክ አሲድ አለመውሰድ፣ እናት ለተደራራቢ የጽኑ ህመሞች ተጋላጭ ከሆነች ምክንያት ሊሆን ይችላል” ተብሎ ይገመታል ሲሉ ተናግረዋል።

የቀዶ ጥገና ህክምና ሲሰራ እና ከተሰራ በኋላ የቡድን ስራ አስፈላጊ በመሆኑ ተከታታይ የሙያ ስልጠና አስፈላጊ ነውም ብለዋል ዶክተር ይገረሙ።

የከንፈር እና ላንቃ ስንጥቃት በሽታ ሳይሆን ህጻናት በእርግዝና ወቅት የሰውነታቸው ክፍል እኩል ሳያድግ ሲቀር የሚፈጠር ነውም ብለዋል።

ነገር ግን ይህ ጉዳይ የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን በህክምና የሚስተካከል ጉዳይ ነው ያሉት ዶክተር ይገረሙ በኢትዮጵያም ህክምናው መሰጠት ከተጀመረ ከ20 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ተናግረዋል።

ህክምናው ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ተደራሽ መሆኑን ዶክተር ይገረሙ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ውስጥ ከሚወለዱ ህጻናት ውስጥ 0.4 በመቶዎቹ ከላንቃ ወይም ከንፈር ስንጥቃት ጋር ይወለዳሉ ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *