ኢትዮጵያ ለሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለሱዳን ጅቡቲ እና ኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል በመሸጥ ላይ ስትሆን ለተጨማሪ ሀገራትም ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ ለይ ትገኛለች፡፡
ከአንድ ወር በፊት በታንዛኒያ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲ የሀይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራርመው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ሀምሌ 2022 ላይ ለ25 ዓመት የሚዘልቅ የሀይል ሽያጭ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት የተደረጉ የሀይል ሽያጭ ስምምነቶች ሳይመረመሩ ተጨማሪ ስምምነቶች እንዳይካሄዱ እገዳ ጥሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በኬንያ መንግስት ላይ እገዳ ጣለው በገጠር ለሚኖረው ህዝብ እየቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል ታሪፍ ውድ ነው በሚል ነው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ለኬንያ ሀይል የምትሸጠው ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ህዝቧ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ውጪ መሆኑ አስተማማኝ ሀይል ለኬንያ ላይቀርብ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በገባችው የሀይል ሽያጭ ውል መሰረት ለኬንያ በቂ ሀይል እያቀረበች እንዳልሆነ የሀገሪቱ ሀይል እና ፖትሮሊየም ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ኬንያ በውሏ መሰረት ከኢትዮጵያ በቂ ሀይል ካልቀረበላት ውሏን ልትሰርዝ እንደምትችልም ባለስልጣኑ አስጠንቅቋል፡፡
ባለስልጣኑ በአዲስ አበባ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ለኬንያ ስጋት እንደሚሆን ያስታወቀ ሲሆን የምንፈልገው ሀይል ካልቀረበልን ውላችንን ልናቋርጥ እንችላለን ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
ኬንያ አንድ ኪሎ ዋት ሀይልን በ6 ነጥብ 5 የአሜሪካ ዶላር ሳንቲም ለመግዛት የተስማማች ሲሆን በ2027 አዲስ ታሪፍ ስምምነት ልትፈራረም እንደምትችልም ተገልጿል፡፡
ኬንያ ከኢትዮጵያ በምትገዛው የኤሌክትሪክ ሀይል እስከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎቿ የሀይል ፍላጎት በመሸፈን ላይ ትገኛለችም ተብሏል፡፡
ይሁንና በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ማጋጠሙ ከኬንያ ጋር ለገባችው የሀይል ሽያጭ ፈተና ሆኗል የተባለ ሲሆን የሀይል መቆራረጥ እና እጥረት በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ላይ ችግሩ በስፋት እንዳለ ተገልጿል፡፡
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል መሰረተ ልማቶቿን ለማዘመን አንድ ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹን ከሰሞኑ ለመስጠት ባንኩ እና የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ባሳለፍነው ሳምንት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ከሰሀራ በረሃ በታች ካሉ ሀገራት ውስጥ የኤሌክትሪክ እጥረት ካለባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ሶተኛዋ ሀገር መሆኗን ባንኩ አስታውቋል፡፡