የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ በቴ ኡርጌሳ ተገደሉ

የተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር / የፖለቲካ ኦፊሰር የሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ትላንትና ለሊት በመቂ ከተማ መገደላቸው ተገልጿል።

“ካረፉበት ሆቴል ውስጥ ትላንት ለሊት ተወስደው ተገድለው ነው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተገኝቷል” ሲል ፓርቲያቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኢነግ በመግለጫው አክሎም አቶ በቴ ኡርጌሳ ከህግ ውጪ በተፈጸመባቸው ግድያ ህይወታቸው ማለፉን ገልጾ ግድያው የኦሮሞን ጥያቄ ለማፈን እና አመራር አልባ ለማድረግ ነው ሲልም ገልጿል፡፡

በኦሮሞ ህዝብ የሚወደዱ ሰዎችን እያሳደዱ መግደል ቀጥሏል ያለው ኦነግ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ተገድሎ እስካሁን ፍትህ አልተጠም ሲልም ፓርቲው አክሏል፡፡

አቶ በቴ ኡርጌሳ በተደጋጋሚ ጊዜ ለእስር ሲዳረጉ የቆዩ ሲሆን በቅርቡም ” ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት ” ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ታስረው በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተለቀው ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ አፋጣኝ፣ ገለልተኛና ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ኮሚሽኑ ከተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አባል በቴ ኡርጌሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ወንጀለኞቹ በህግ እንዲጠየቁ በሁለቱም በኦሮሚያ ክልል እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ባለስልጣናት አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና ሙሉ_ምርመራ እንዲደረግ ይጠይቃል” ብለዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር አቶ ጃዋር መሀመድ በበኩላቸው ” የትኛው እጅ ነው ጨክኖ በቴ ኡርጌሳን በለሊት ከእንቅልፋቸው አስነስቶ የሚረሽነው? እንዴትስ በቴን የሚያውቅ ሆዱ አስችሎት አይኑ እያያ  ሊገድለው ቻለ? ወገኖች ይህ ምን ይባላል አሁን ?

በቴን ቢያንስ አውቀዋለሁ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ አቋም ቢኖረውም ለማንም ሆነ ለየትኛውም ቡድን ክፉ የሚያስብ ሰው አልነበረም።

እ.ኤ.አ ነሀሴ 2016 በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ተይዞ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበት ሞተ ተብሎ ለረጅም ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ ቆይቷል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእስርና ለእንግልት ቢዳረግም የበቀል ሰው አልነበረም። ይህ ለበቴ አይገባም ነበር። ” ሲሉ የአቶ በቴን ግድያ አውግዘዋል።

የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ትላንት ለሊት በትውልድ ከተማቸው መቂ ካረፉትበት ሆቴል ተውስደው ተገድለው መንገድ ላይ ተጥለው ተገኝተዋል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *