የኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ ዉይይት ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት እና ሀገራት ጋር እያደረገችው ያለው ውይይት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋሙ አይኤምኤፍ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይቶችን ከሚያደርጉ አበዳሪ ተቋማት መካከል ዋነኛው ሲሆን ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ቆይታ አድርጎ መመለሱ ተገልጿል፡፡

አይኤምኤፍ በድረገጹ ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መሰረት ከመጋቢት 10 እስከ 24 ቀን 2016 ዓም ድረስ በአዲስ አበባ ቆይታ አድርጎ ተመልሷል፡፡

ኢትዮጵያ ልታካሂደው ባሰበችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ አይኤምኤፍ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ እንዳቀረበች የገለጸው ይሄው ተቋም በአልቫሮ ፒሪስ የተመራ የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ቡድን ወደ አዲ አበባ መምጣቱን አስታውቋል፡፡

ለ15 ቀናት በዘለቀው በዚህ የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ቡድን እና የኢትዮጵያ ባለሙያዎች እና ባለስልጣናት መካከል የተደረገው ውይይት ገንቢ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ይሁንና አይኤምኤፍ እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተጨማሪ ውይይት በአሜሪካ ዋሸንግተን እንደሚካሄድም የአይኤም ኤፍ መግለጫ ያስረዳል፡፡

ሮይተርስ በበኩሉ አይኤምኤፍ እና ኢትዮጵያ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ገልጾ ሁለቱ አካላት ያልተስማሙባቸውን ጉዳዮች አልጠቀሰም፡፡

ቻይናን ያላካተተው የአበዳሪ ሀገራት እና ተቋማት ስብስብ የሆነው ፓሪስ ክለብ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ጋር በፈረንጆቹ እስከ መጋቢት 31 ድረስ ስምምነት ላይ እንድትደርስ የሰጠው ጊዜ ተጠናቋል፡፡

ይሁንና በዚህ የጊዜ መጠናቀቅ ሁኔታ ኢትዮጵያም ሆነች የፓሪስ ክለብ እስካሁን በይፋ መረጃ አልሰጡም፡፡

ኢትዮጵያ ከ11 ዓመት በፊት በዩሮ ቦንድ የገዛችውን አንድ ቢሊዮን ዩሮ መክፈል ባለመጀመሯ ምክንያት ከጋና እና ዛምቢያ በመቀጠል ሶስተኛ ሀገር መባሏ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የዩሮ ቦንድ ብድሩን መክፈል ያልጀመርነው በገንዘብ እጥረት ሳይሆን ሁሉንም አበዳሪዎቻችንን እኩል ማየት አለብን ብለን ስለምናምን ነው ስትል ምላሽ መስጠቷ አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ያለባት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹ ከቻይና የተገኘ ሲሆን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላት በመጠየቅ ለይ ትገኛለች፡፡

የብድር ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከቻይና ውጪ ያሉ ሀገራ እና አበዳሪ ተቋማት የብድር መክፈያ ጊዜን እስካሁን ለማራዘም ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ ከታማኝ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከፍላለች ብለዋል፡፡

ጦርነት፣ ኮሮና ቫይረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኑሮ ውድነት እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየፈተኑ ያሉ ክስተቶች ሲሆኑ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ቢቆምም ሌላ ጦርነት በአማራ ክልል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *