መንግስት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን መቆጣጠር የሚያስችለውን ህግ አወጣ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን አጽድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ መንገግስት የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ቢሆንም፤ ከመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም ብለዋል።

አቶ ተስፋዬ አክለውም ፤ በኢትዮጵያ የተጋነኑ እና ከተከራዮች የመክፈል አቅም በላይ የሆነ የቤት ኪራይ ጭማሪዎች በከተሞች እንዳሉ ተናገረዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የከተማ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ እና ዜጎችም ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

በተለይም በከተሞች አካባቢ የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ቁልፍ ችግሮች መካከል ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ አንዱ እንደሆነ መንግስት ያምናል ብለዋል።

ለዚህም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግስት አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መንግስት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን መቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ ግልጽ እና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይ መብትን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተናገድ ስርዓት መዘርጋ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል። 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አዋጁን በሚመለከት ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ ፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የመንግስት ሰራተኞችና የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የተዘጋጀ አዋጅ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ከ25 እስከ 30 በመቶ በላይ ለቤት ኪራይ ማዋል እንደማይጠበቅባቸው የገለጹት ወ/ሮ ጫልቱ፤ ይህ አዋጅ አንድ ተከራይ ለ2 ዓመት ያክል ያለምንም ጭማሪ በተከራየው ቤት ውስጥ ተረጋግቶ የመኖር መብት ይሰጠዋል ብለዋል።

የፍትህ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው አዋጁ በአከራዩ እና በተከራዩ መካከል አለመግባባት ካለ በተቆጣጣሪው አካል በሚደረግ አስተዳደራዊ ፍትህ የሚቀረፍ እንጂ በቀጥታ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንደማይታይ ገልጸዋል።

አዋጁ የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑና ዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ለከተማ መስተዳድሮችና ለክልሎች እንደሚሰጥም ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየትም፤ አዋጁ በሀገሪቱ ከቤት ኪራይ ጋር ተያያዞ የሚስተዋሉ ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስቀር እምነታቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን የነበረው አካሄድ ስርዓት ያልነበረው እና የአከራይን መብት የበለጠ የሚደገፍ ነበር ያሉት የምክር ቤቱ አባል፤ አዲሱ አዋጅ የተከራይ እና አካራይ መብት ሚዛናዊ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት አከራዮች በፈለጉት ጊዜ ዋጋ ይጨምሩ ነበር፤ አሁን በጸደቀው አዋጅ ተቆጣጣሪ አካል በአመት አንድ ጊዜ በመንግስት በኩል የሀገሪቱን እና የኢኮኖሚዉን ነባራዊ ሁኔታ ታይቶ በመቶኛ በሚወስነው መሰረት የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተደንግጓል።

አከራይ ለተከራይ ሊጠይቅ የሚገባው ክፍያ ከሁለት ወር ያልበለጠ እንዲሆን እንዲሁም አካራይ ተከራይ ቤቱን እንዲለቅ ሲፈልግ ሁለት ወር አስቀድሞ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ተደንግጓል።

የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ላይ ከተወያዩ በኋላ መኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን በሶስት ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

ኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድ ከሆኑባቸው የአፍሪካ ሀገራት ከካሜሩን በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር ስትሆን ዜጎች 43 በመቶ ገቢያቸውን ለቤት ኪራይ ያወጣሉ፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *