የአዲስ አበባ እምብርት ከምትባለው ፒያሳ 11 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን ከንቲባ አዳነች ተናገሩ

በአዲስ አበባ ከፒያሳ እና አካባቢው ከሳምንታት በፊት በተጀመረው የከተማ ማስዋብ ግንባታ ምክንያት 11 ሺህ ሰዎች መነሳታቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በሁሉም የመንግስት ሚዲያዎች በተላለፈ ንግግራቸው ላይ እንዳሉት “በድምሩ ወደ 11 ሺህ ሰው ይሆናል ከዚያ አካባቢ ወደተሻለ ቦታ የወሰድነው” ብለዋል።

ነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰው በፒያሳ አካባቢ ካሉት ራስ መኮንን ድልድይ፣ ማህሙድ ሙዚቃ ቤት፣ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ፣ አራት ኪሎ የሚገኘው አብርሆት ቤተ መጽሐፍት፣ ቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ቸርችል ጎዳና ድረስ በሚያካልለው “የኮሪደር ልማት” ምክንያት የተነሱ ናቸው።

ይህ የኮሪደር ልማት ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ባለው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ 8.1 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንም ከንቲባዋ ገልጸዋል። አዳነች በዚህ ሪፖርት ላይ ከተነሺዎቹ መካከል 1 ሺህ 989 ያህሉ የቀበሌ ቤቶች ናቸውም  ብለዋል።

ቀድሞ ኪራይ ቤቶች አጀንሲ አሁን የቤቶች ኮርፖሬሽን የተባለው ተቋም በሚያስተዳድራቸው 490 ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ከአካባቢው ተነስተዋል። ከንቲባዋ ከመንግሥት ቤቶች በተጨማሪ የግል የመኖሪያ፣ የንግድ እና የእምነቶች ቤቶች መነሳታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በድምሩ 300 እንደሆኑም አስረድተዋል።

ሆኖም የትኞቹ የእምነት ተቋሞች እንዲነሱ እንደተደረገ የገለጹት ነገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 886 ሼዶች፣ ኮንቴይነሮች እና ተለጣፊ ሱቆችም ፈርሰዋል። በተጨማሪም “ለጊዜው” ተብለው የተገነቡ 89 መጠለያዎች መነሳታቸውን ከንቲባዋ አስረድተዋል።

ከመኖሪያ፣ ከንግድ እና ከእምነት ቤቶች በተጨማሪ አጥሮች፣ የእግረኛ ማቋረጫ ድልድይ፣ የመብራት፣ የውሃ እና የስልክ መስመሮችን ጨምሮ በርካታ መሠረተ ልማት መነሳታቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል። ከንቲባ አዳነች ከአካባቢው ከተነሱት 11 ሺህ ነዋሪዎች ውስጥ 619 የሚሆኑት ተማሪዎች እንደሆኑም አመልክተዋል።

ከአካባቢዎቹ የተነሱት ነዋሪዎች እንደምርጫቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ወይም የቀበሌ ቤት እንደተሰጣቸውም ከንቲባዋ በሪፓርታቸው ላይ ገልጸዋል። በቤቶች ኮርፖሬሽን ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ደግሞ በተቋሙ አማካኝነት ሌላ ቤት ለኪራይ ቀርቦላቸዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ ለንግድ ተቋማትም ምትክ ቦታ ወይም በቦታው ላይ እንዲያለሙ ዕድል መስጠቱን ከንቲባዋ አስረድተዋል። መንግሥት በአካባቢው ለልማት የሚፈልጋቸውን ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የማፍረስ ዕቅድ እንዳለው ያነሱ ሲሆን፣ እስካሁን 71 በመቶ ያህል መነሳቱንም ይፋ አድርገዋል።

ከንቲባ አዳነች በአካባቢው ምንም አይነት ህንጻ እንደማይፈርስ ተናግረው፤ ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ 102 ህንጻዎች መንግሥት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት እንደሚታደሱ አመልክተዋል። “በምን ዓይነት ማቴሪያል ነው መታደስ ያለበት? ምን ዓይነት መብራት ነው ሊኖረው የሚገባው? ምን ዓይነት ቀለም ነው ሊቀባ የሚገባው. . . የሚለውን በተመለከተ ጥናት ተደርጎ በዚያ መሠረት እንዲያድሱ መልሰን ሰጥተናቸዋል” ብለዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የተመዘገቡ ስድስት ቅርሶች እንደሚገኙ የተናገሩት አዳነች አቤቤ “እነሱን ባሉበት ቦታ የማደስ፣ የማሳመር የበለጠ ቅርስነታቸው ጎልቶ ከአድዋ ጋር ታሪካቸው ተያይዞ ለቱሪስት መስህብ መሆን እንዲችሉ ብቁ የማድረግ ሥራ እንሠራለን” ብለዋል።

ከአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ሲነሱ ተደጋጋሚ ውይይት እንደተደረገ የተናገሩት ከንቲባዋ፣ በአካባቢው መፍረስ ላይ “አንድም ሰው” ቅሬታ አላነሳም ብለዋል።

ይሁንና ከተማዋን ለማስዋብ በሚል ለመልሶ ማልማት ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው በሶስት ቀናት ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት ከኖርንበት ቤታችን እንድንወጣ እና እንድናፈርስ መታዛዘችን አግባብ አልነበረም ብለዋል፡፡

ሶስት ቀናት ለዓመታት የኖርንበትን ቤት ለማፍረስ አይደለም እቃችንን ለማስተካከል እንኳን በቂ አልነበረም ያሉት እነዚህ ነዋሪዎች ለኢኮኖሚ መቃወስ፣ ልጆች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ፣ አብረን ከኖርናቸው ጎረቤቶቻችን እና ጓደኞቻችን ጋር እንድንራራቅ እና ከስራ እንድንፈናቀል አድርጎናልም ብለዋል፡፡

ታዋቂው ኢኮኖሚስት ሙሼ ሰሙ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከፒያሳ እና አካባቢው መንግስት በተከተለው የመልሳ ማልማት ፕሮግራም ምክንያት በትንሹ 500 ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *