በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ቦታዎች ቀጣዮቹ ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ ይጠናከራል ተብሏል፡፡
በመጪዎቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ እየተጠናከረና እየተስፋፋ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም አስታውቋል።
በተጨማሪም በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት ምስራቅ ሸዋ፣ አዲስ አበባ፣ ምስራቅ አማራ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ እና አይሻ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቅሷል።
ከኦሮሚያ ክልል የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፥ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።
በተመሳሳይ የአፋር ክልል ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፣ የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የሶማሌ ክልል ዞኖች ተመሳሳይ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።
በተጨማሪም ከአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ፣ የመካከለኛው እና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የዋግኸምራ ዞኖች፣ ከጋምቤላ ክልል የአኝዋክ እና የመዥንግ ዞኖች፣ ከቤኒሻንጉል ክልል የአሶሳ፣ የማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ፣ ከትግራይ ክልል የመካከለኛው ትግራይ ዞን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት ድርቅ የሚከሰት ሲሆን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለእርዳታ ይዳረጋሉ፡፡
በተለይም በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል በሶማሊ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞኖች እንዲሁም በደቡባዊ ኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያቶች ለእርዳታ የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ በመምጣት ላይ ይገኛል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን እንዲሁም 21 ህጻናት ደግሞ ህይወታቸው አልፎ መወለዳቸውን አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ አደጋ እና ሥራ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ብቻ 4 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቁን ይታወሳል።