የፍትህ ሚኒስቴር በእነ ክርስቲያን ታደለ መዝገብ ባሉ 52 ተጠርጣሪዎች ላይ የፖለቲካ ርዕዮትን በሀይል ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፣ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ እንዲሁም የሽብር ወንጀሎችን ለመከላከል የወጣውን ህግ ጥሰዋል በሚል ክስ መስርቷል፡፡
በዚህ ክስ መዝገብ ስርም ክርስቲያን ታደለ፣ ዮሀንስ ቧያለው፣ ካሳ ተሸገር (ዶ/ር) ጫኔ ከበደ፣ እስክንድር ነጋ፣ ዘመነ ካሴ፣ አበበ ፈንታው፣ አሰግድ መኮንን፣ መከታው ማሞ፣ ፈንታሁን ሙሃባ እና ሌሎችም ተካተዋል፡፡
ከ52ቱ ተከሳሾች መካከል 14ቱ ተጠርጣሪዎች ልደታ በሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህገ መንግስት እና ሽብር ወንጀሎች ችሎት የቀረቡ ሲሆን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ እና ቤተሰቦች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለአልዐይን እንዳሉት በችሎቱ መገኘታቸውን ገልጸው ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ማንነት ካረጋገጠ በኋላ የተለያዩ ትዕዛዞችን አስተላልፏል ብለዋል፡፡
በችሎቱ ከተላለፉ ትዕዛዞች መካከልም አቃቢ ህግ ተከሳሾች አሁን ካሉበት የፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ ወደ ማረሚያ ቤት ይዛወሩ፣ ክሱም መታየት ይጀምር ብሎ ለፍርድ ቤት ዳኞች አቅርቦ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የተከሳሾች ጠበቃም ተከሳሾች ላለፉት ስምንት ወራት በተለያዩ ቦታዎች በእስር ላይ ከህግ ምክር እና አገልግሎት ተገልለው በመቆየታቸው ያሉበት ሁኔታ ሳይረጋገጥ ወደ ማረሚያ ቤት መዛወር እና የክስ ሂደቱም ለተለዋጭ ቀጠሮ ችንዲተላለፍ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡
እንዲሁም ዛሬ ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች በአቶ ዩሃንስ በኋያለው አማካኝነት የነበሩበትን ሁኔታ ለችሎቱ እንዲያስረዱ ችሎቱ እንዲፈቅድላቸው እና ተግዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱም ይህን እድል ሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡
አቶ ዩሃንስ ቧያለውም ላለፉት ስምንት ወራት በአዋሽ አርባ እና አዲስ አበባ በጨለማ ክፍል ውስጥ እንደታሰሩ፣ ለመንቀሳቀስ አመቺ ባልሆነ ስፍራ መታሰራቸውን፣ ህክምናን ጨምሮ የሀይማኖት አባት፣ ቤተሰብ እና የህግ ማማከር አገልግሎት ተከልክለው መቆየታቸውን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹን አጅቦ ወደ ፍርድ ቤት ያመጣቸውን የፌደራል ፖሊስ ሀላፊ በተከሳሾች በተነሱ ቅሬታዎች ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቁን፣ የፖሊስ ሀላፊውም በተከሳሾች ከተነሱት መካከል የተወሰኑ አገልግሎቶችን የከለከልናቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለማይፈቅድላቸው በመሆኑ እንደሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ግራ እና ቀኙን ያዳመጠው ችሎቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤት ከቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳያቸው በመደበኛ የህግ አሰራር መሰረት የሚዳኝ በመሆኑ ማንኛውም ተጠርጣሪ እና ተከሳሽ በህጉ መሰረት የተፈቀደለትን መብት መከልከል እንደማይቻል ትዕዛዝ መስጠቱን የተከሳሾች ጠበቃ ሰለሞን ነግረውናል፡፡
እንዲሁም ተከሳሾች ተጨማሪ ጥያቄ ካላቸው በጠበቃቸው በኩል ለፍድ ቤቱ ማቅረብ እንደሚችሉም ችሎቱ ትዕዛዝ እንደሰጠ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት ሳይሄዱ አሁን ባሉበት የፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ እንዲቆዩ ቀጣይ የክስ ሂደቶችን ለማየትም ለመጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም መቀጠሩን ጠበቃ ሰለሞን አክለዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስም በአቃቢ ህግ ክስ መዝገቡ ከተጠቀሱት 52 ተጠርጣሪዎች መካከልም እስካሁን ያልተያዙ ቀሪ 38 ተጠርጣሪዎችን ይዞ እንዲያቀርብም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡