ኢትዮጵያ ከማዕድን ንግድ ከ252 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘሁ አለች

በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ከማዕድን ዘርፍ 252 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት የተለያዩ ዓይነት ማዕድናት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 252 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

ባለፉት ስምንት ወራት ከሁለት ሺህ 673 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ፣ 66 ቶን በላይ ታንታለም እና ከ11 ሺህ 176 ቶን በላይ ሉቲየም ኦር ለውጭ ገበያ መቅረባቸውን ዘርዝረዋል።

በተጨማሪም ከ99 ሺህ 021 በላይ ቶን የጌጣጌጥ እንዲሁም 29 ሺህ 281 ቶን በላይ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል።

የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አቶ ሚሊዮን አክለውም፤ ሀገሪቷ ከማዕድን ዘርፍ ባላት አቅም ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፤ በዘርፉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቅ የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በባሕላዊ ማዕድን አምራቾች ተመርቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ማዕድናት ተገቢውን ዋጋና የጥራት ደረጃ እንዲይዙ ተደርጓል።

በተጨማሪም ተኪ ምርቶችን ከማሳደግ አኳያ የድንጋይ ከሰል እጥበት፣ የሴራሚክ ምርት፣ ማርብል፣ ግራናይትና ቴራዞ ምርት ውጤቶች ላይ ለተሠማሩ ኩባንያዎች አፈፃፀማቸው ከፍ እንዲል የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ተከናውኗል።

ወሳኝ በሆኑ ማዕድናት ለአብነትም ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰልና የጌጣጌጥ ማዕድናት በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል የስትራቴጂ ሰነዶች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በዘርፉ የገበያ ትስስር ለማጠናከርና የኢትዮጵያ ማዕድናት ተፈላጊነት ለማሳደግ ጥረት መደረጉን ጠቅሰው፤ በዚህም የማዕድን ኤክስፖ በማዘጋጀት በሀገሪቱ ያለውን ሃብት የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። እንዲሁም በላኪዎች በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ ኤክስፖዎች ላይ በመሳተፍ ማስተዋወቅ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ማዕድናትን አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድ የኢንዱስትሪ ማዕድናት በመጠንና በአይነት ዕድገት አሳይቷል፤ ለአብነትም ሉቲየምና ኢንደስትሪያል ኳርትዝ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በዘርፉ በቀጥታ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ጠቁመዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *