የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አምስት ተጨማሪ የአገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አሁን ላይ አየር መንገዱ 136 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት የጠቆሙት ስራ አስፈጻሚው ተጨማሪ የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አምስት የአገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤርፖርቶቹ የሚገነቡት በሚዛን ቴፒ አማን፣ ያቤሎ፣ ጎሬ፣ መቱና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውን ገልጸው፤ አራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።
ይህም በአገር ውስጥ ያሉ ደንበኞች ፍላጎት ተከትሎ የሚተገበር መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ሌሎች መዳረሻዎችን ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ ግንባታቸው እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ጉዳት የደረሰበት የአክሱም ኤርፖርት እና በሶማሊ ክልል የሚገኘው የቀብሪደሃር ኤርፖርት እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡም ወደ ሥራ እንደሚገቡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ አዲሱን 5 ቢሊየን ዶላር ሚያወጣ ‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተማ’ ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
አየር መንገዱ “ኤርፖርት ሲቲ” ብሎ የሚጠራውን ግንባታ ለመጀመር ከጫፍ የደረሰው እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማርካት መሆኑን የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ለማ ያደቻ ተናግረዋል፡፡
የ ‘አየር መንገድ ከተማው’ ካልተገነባ ዓየር መንገዱ በዘርፉ እያስመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገት አንጻር እንደሚፈተን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፕሮጀክቱ መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 5 ቢሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፥ በዓመት 100 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አሁን ላይ ዓየር መንገዱ በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ጥቂት ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ የመጀመሪያውን የ ‘ዓየር መንገድ ከተማ’ ግንባታ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ሆቴሎች ፣አፓርትመንቶች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
የአዋጭነት ጥናቱን በማጠናቀቅም ለዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ ከቦይንግ እና ኤርባስ የአቪዬሽን ተቋማት 78 አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማቱ ይታወሳል፡፡