ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የነበረ ሲሆን አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም፡፡
በዚህ ጦርነት ምክንትም ከስድስት ሺህ በላይ የሆኑ ሰራተኞች ስራ ማቆም እና ቤተሰቦቻቸውን መመገብ አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ከሥራ ውጭ የኾኑ ዜጎች፣ በግጭቱ ምክንያት ይሠሩባቸው የነበሩ ተቋማት በመዘጋታቸው፣ ካለፉት ሰባት ወራት ወዲህ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደተጋለጡ አመልክተዋል፡፡
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት በጦርነቱ ምክንያት ከ1 ሺህ 200 በላይ በኾኑ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ከስድስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ከሥራ ገበታ ውጭ ሆነዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በዚህ ጦርነት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ15 ቢሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ ንብረት ወድሟል ብለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ በክልሉ በተከሰተዉ ጦርነት 298 ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሲሆኑ 3725 ትምህርት ቤቶች ደግሞ እንደተዘጉ ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል መናገሻ ባህር ዳር ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጪ ገድሏል ሲል ከሷል፡፡
ድርጅቱ በሪፖርቱ እክሎም በባህር ዳር ከተማ ውስጥ አቡነ ሃራ፣ ልደታ እና ሳባ ታሚት በተባሉ አካባቢዎች ከ17 በላይ ንጹሃን በመከላከያ ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ከአይን እማኞች ማረጋገጡን እና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች ሟቾቹን ለመቅበር እንኳን እንዳልተፈቀደላቸው አብራርቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ከሁለት ወር በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት መራዊ ከተማ ከ45 በላይ ንጹሃንን ተኩሰው እንደገደሉ በባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በመራዊ ከተማ የተፈጸመው የንጹሃን ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ያሳሰቡ ቢሆንም የፌደራል መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው ምላሽ መከላከያ ሰራዊት የወሰደው እርምጃ ራሱን ለመከላከል ሲል እንደሆነ እና ጉዳዩም በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንደማይደረግ አስታውቋል፡፡