ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሁለት ዓመት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጎን ቆመው እየተዋጉ ያሉ ቅጥረኛ ወታደሮችን ማንነት ይፋ አድርጋለች።
እንደ ሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር መረጃ ከሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ከዩክሬን ጎን ሆኖ ሩሲያን እየወጋ ይገኛል ተብሏል።
ይህ ኢትዮጵያዊ እስካሁን በህይወት እንዳለ የተገለጸ ሲሆን ወታደሩ ኢትዮጵያዊ ከመሆኑ ውጪ ማንነቱ ይፋ አልተደረገም።
በአጠቃላይ ይህ ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ89 ሀገራት የተውጣጡ 13 ሺህ 387 ቅጥረኛ ወታደሮች ከዩክሬን ጎን ተሰልፈዋል።
ከጠቅላላው ቅጥረኛ ወታደሮች ውስጥም 5 ሺህ 962 ያህሉ በሩሲያ ጦር መገደላቸው ተገልጿል።
ፖላንድ ቅጥረኛ ወታደሮችን በማዋጣት ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን 2 ሺህ 960 ዎቹ ተገድለዋል ተብሏል።
ከፖላንድ በመቀጠል አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጆርጂያ እና ብሪታንያ ብዙ ዜጎቻቸው ከዩክሬን ጎን የቆሙ በቅጥረኛ ወታደርነት የተመዘገቡ ሀገራት ናቸው።
ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 ሀገራት የተውጣጡ 249 ወታደሮች ከዩክሬን ጎን ሆነዋል የተባለ ሲሆን 103 ያህሉ መገደላቸው ተገልጿል።
ናይጀሪያ፣ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በአንጻራዊነት ብዙ ዜጎቻቸው ለዩክሬን በቅጥረኛ ወታደርነት የተመዘገቡባቸው ሀገራት ናቸው።
ዩክሬን ከሩሲያ ወታደሮች የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ስትሆን የሰሜን ትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ አባላት ዋነኛ አጋሮቿ ሆነዋል፡፡
የኔቶ አባል ሀገራት እና አውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን ከማዋጣት ባለፈ ወታደራዊ መረጃዎችን እና የሩሲያ ኢኮኖሚ እንዲጎዳ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
ሁለት ዓመት ባለፈው በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊን ሲሰደዱ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው መሰረተ ልማቶችም ወድመዋል ሲል የዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስደተኞች ኮሚሽን ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ብሪታንያ ሩሲያ በየዕለቱ አንድ ሺህ ወታደሮቿን እያጣች እንደሆነ ከአንድ ወር በፊት የገለጸች ሲሆን በአጠቃላይም 400 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን አስታውቃለች፡፡