ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ጀነራል ክንፈ ዳኘው እና አብዲ ኢሌ ከእስር ተፈቱ

በ2013 በተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በባህርዳር ከተማ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው የተመረጡት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ታስረው ነበር፡፡

ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ እንዳሉት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በመታወቂያ ዋስትና ከእስር ተለቀዋል።

የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ከሁለት ወራት በፊት በጸጥታ ሀይሎች ተይዘው የታሰሩ ቢሆንም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቆይተው ዛሬ ከእስር ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ በተመሳሳይ ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጽታ ሀይሎች ተወስደው በእስር ላይ የነበሩት ሌላኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብታቸው ከታሰሩ ከሰባት ወራት በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተነስቷል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊትም የአዲስ አበባ እና አማራ ክልል ምክር ቤቶች የካሳ ተሻገር (ዶ/ር) እና አቶ ዮሀንስ ቧያለው ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳታቸው አይዘነጋም፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡

ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ቢሆንም አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የቀድሞው የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ከእስር ተፈተዋል።

ከ6 ዓመት በፊት ነሐሴ 21/2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው አስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከእስር የተለቀቁት ዐቃቤ ሕግ ክሱን በማንሳቱ መሆኑን ጠበቃቸው ገልጸዋል።

ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው እስክንድር ገዛኸኝ ፤ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክሳቸው ተነስቶ የተለቀቁት ዛሬ መጋቢት 5/2016 ዓ.ም መሆኑን አመልክተዋል።

ከአቶ አብዲ በተጨማሪም በተመሳሳይ በእሳቸው የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ የሌሎችም ተከሳሾች ክስ ተቋርጦ መለቀቃቸውን ጠበቃቸው አክለዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *