ሶማሊያ እና ቱርክ የጋዝ እና ነዳጅ ልማት ሰምምነት ተፈራረመሙ

 ቱርክ ከሶማሊያ ጋር በውቅያኖስ ውስጥ ጋዝ እና ነዳጅ ለማልማት በትናንትናው እለት ስምምነት ማድረጓን የቱርክ የኢነርጂ ሚኒስትር ተናግረዋል።

ይህ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት ባለፈው ወር ከተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት የቀጠለ እና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክር ነው ተብሏል።

ስምምነቱ በሁለቱ መንግስታት መካከል የተፈረመ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በሶማሊያ መሬት እና ውሃማ አካላት ውስጥ ነዳጅ መፈለግን እና ማምረትን የሚያካትት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

በስምምነቱ መሰረት የሶማሊያ ሀብት ለሶማሊያውያን ለማዋል እና በአፍሪካ ቀንድ የቱርክን ተጽዕኖ ከፍ ለማድረግ አላማ እንዳላቸው ሚኒስትሩ አልፓርስላን ባይራክታር ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የሶማሊያ ድንበር በሙሉ ለቱርክ መሸጡ ያስቆጣቸው ሶማሊያዊያን በሞቃዲሾ የተቃውሞ ሰልፍ መውጣታቸውን የሶማሊያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ከሁለት ወር በፊት የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ውጥረት አስከትሏል፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ ባህር ላይ የባህር በር እንድታገኝ የሚፈቅድ ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ለሶማሊላድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚል ተካቶበታል፡፡

ሶማሊያ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላድ ስምምነት መበሳጨቷን የገለጸች ሲሆን ይህ ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን የተለያዩ ጥረቶችን በማድግ ላይ ትገኛለች፡፡

ሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ አረብ ሊግ እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ወይም ኢጋድ በዚህ ስምምነት ዙሪያ እንዲወያዩ እና ውሳኔ እንዲያሳልፉ ጥያቄ አቅርባለች፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረምኩት የመግባቢያ ስምምነት የየትኛውንም ሀገር ሉዓላዊነት አልጣሰም ሌሎች ሀገራት የሚያደርጉትን እንዳደረገች አስታውቃለች፡፡

ሶማሊያ የባህር በሯን በቱርክ ለማስጠበቅ በሚል ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን በዚህ ስምምነት መሰረትም ቱርክ የሶማሊን ባህር ትጠብቃለች፡፡

ኢትዮጵያ የሶማሊያ እና ቱርክ ስምምነት ዙሪያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ለመፈጸም እንቅፋት አይፈጥርም በሚል ለቀረበው ጥያቄ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት አያሳስበኝም ብላለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም እንዳሉት ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላት፣ ቱርክ እና ሶማሊያ ሉዓላዊ ሀገራት በመሆናቸው የፈለጉትን ስምምነት ከየትኛውም ሀገር ጋር የማድረግ መብት አላቸው ብለዋል፡፡

የሶማሊያ እና ቱርክ ወታደራዊ ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ እንዳልሆነም አምባሳደር መለስ ዓለም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *