በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት 15 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት መውደሙ ተገለጸ

ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡

ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የነበረ ሲሆን አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም፡፡

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊና የኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በዚህ ጦርነት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከ15 ቢሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ ንብረት ወድሟል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ መሆን እንደሚገባ አቋም ወስዶ እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ደሳለኝ ጦርነት በጦርነት እንደማይጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ያምናልም ብለዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እያደረሱ ነው የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “የጸጥታ ሀይሎች ንጹሃንን ከጥቃት በጠበቀ መንገድ በጥንቃቄ እያከናወኑ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጦር ሀይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በአዲስ አበባ በተከበረው 128ኛው የአድዋ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር አዲስ አበባ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንገባለን ሲሉ የነበሩ ህልመኞችን እቅድ አክሽፈናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል መናገሻ ባህር ዳር ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጪ ገድሏል ሲል ከሷል፡፡

ድርጅቱ በሪፖርቱ እክሎም በባህር ዳር ከተማ ውስጥ አቡነ ሃራ፣ ልደታ እና ሳባ ታሚት በተባሉ አካባቢዎች ከ17 በላይ ንጹሃን በመከላከያ ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ከአይን እማኞች ማረጋገጡን እና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች ሟቾቹን ለመቅበር እንኳን እንዳልተፈቀደላቸው አብራርቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ከአንድ ወር በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት መራዊ ከተማ ከ45 በላይ ንጹሃንን ተኩሰው እንደገደሉ በባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በመራዊ ከተማ የተፈጸመው የንጹሃን ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ያሳሰቡ ቢሆንም የፌደራል መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው ምላሽ መከላከያ ሰራዊት የወሰደው እርምጃ ራሱን ለመከላከል ሲል እንደሆነ እና ጉዳዩም በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንደማይደረግ አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *