የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ስራዎች ብቻ ቀርተውታል ተባለ

ከ13 ዓመት በፊት የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባት ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ስራው ግንባታ የደረሰበት ደረጃ 98 ነጥብ 9 በመቶ ተጠናቋል የተባለ ሲሆን የኤሌክትሮ መካኒካ ስራው ደውም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ከአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴው ግድብ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ ይገኛል፡፡

የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ አብርሃም የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት አስመልክቶ እንደተናገሩት አሁን ላይ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተመረተ ያለው ኤሌትሪክ ኃይል በ2 ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት መሆኑን ያነሱ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚያመርተው ኤሌክትሪክ ኃይል 5ሺ150 ሜጋ ዋት ይደርሳል፡፡

አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዉብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመንግስት እና ህዝብ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ643 ሚሊዮን  ብር በላይ ከህዝቡ መሰብሰቡን አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም አንስቶ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጪ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች 19 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የህዳሴው ግድብ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።

የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንዳሉት በግድቡ ላይ የኤሌክትሮ መካኒካል ተከላዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸው ግድቡ አሁን ላይ በኹለት ዩኒቶች ሀይል እያመነጨ እንደሚገኝና በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ተጨማሪ አምስት ዩኒቶች ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡

በሀይል ማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው የሕዳሴው ግድብ በአጠቃላይ ሀይል የሚያመነጩ ሰባት ዩኒቶች ይኖሩታል ተብሏል።

ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በአባይ (ናይል) ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን ግድብ የግድቡ ግንባታ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እየተቃወሙ ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት የተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡

ግብጽ ለሶስትዮሽ ድርደሩ ኢትዮጵያን ተጠያቂ ስታደርግ ኢትዮጵያ በበኩሏ ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ውሎች እንዲቀጥሉ ስለምትፈልግ እንዳልተሳካ አሳውቃለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *