በኢትዮጵያ ሶስት ቦታዎች በተከሰተ የትራፊክ አደጋ የ24 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡

በትናንትናው ዕለት በዱከም፣ በወላይታ እና ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በደረሱ ሶስት የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት የ24 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

አደጋዎቹ የደረሱባቸው ኮሙንኬሽን ጽህፈት ቤቶች ባወጡት መረጃ መሰረት የትራፊክ አደጋዎቼ ሰቅጣጭ የሚባሉ ናቸው የተባለ ሲሆን በአጠቃላይ ከ24 ሰዎች ህይወት ማለፍ በተጨማሪ 20 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ዱከም ክፍለ ከተማ የደረሰው የትራፊክ አደጋ አንድ ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ከሁለት ሚኒባሶች እና አንድ ላንድ ክሮዘር ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ አደጋው ደርሷል ተብሏል፡፡

በዚህ አደጋ የ7 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 11 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በቢሾፍቱ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ሌላኛው የትራፊክ አደጋ የተከሰተው በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ሲሆን አደጋው ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ ይጓዝ የነበረ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ 7 ሰዎችን ከጫነ ባለ ሶት እግር ሞተር ወይም ባጃጅ ጋር በመጋጨቱ ተከስቷል፡፡

በዚህ አደጋ የ6 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ አካል ጉዳት አጋጥሟል ተብሏል፡፡

ሌላኛው አደጋ መነሻውን አርባ ምንጭ ከተማ አድርጎ ወደ ሐዋሳ እየተጓዘ የነበረ ተሽከርካሪ በዎላይታ ዞን በዱጉና ፋንጎ ወረዳ ፋንጎ ኮይሻ ቀበሌ ልዩ ቦታው ዞንጋ በሚባል ቦታ የተከሰተ ነው፡፡

በዚህ አደጋ ምክንያት የ11 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሰባት ሰዎች ደግሞ ከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት አጋጥሟቸው በሐዋሳ ከተማ ባሉ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ለሶስቱም የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት እስካሁን ይፋ ያልተደረገ ሲሆን ፖሊስ የአደጋዎቹን መነሻ እያጣራ ነው ተብሏል፡፡

በአደጋው ምክንያት ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና በጽኑ ህክምና ላይ ያሉ ሰዎች ህይወት ሊያልፍ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *