በትግራይ ክልል የኤች አይ ቪ ስርጭት ወደ ከፋ ደረጃ መሻገሩን ክልሉ አስታወቀ

በትግራይ ክልል ባለው አሁናዊ ሁኔታ የህጻናት የተጓዳኝ በሽታ መድኃኒት እና   የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪት  እጥረት መኖሩን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ አሰታወቀ፡፡

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የዘርፈ ብዙ ምላሽ የኤች አይ ቪ  መከላከል እና መቆጣጠር ስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፍሥሀ ብርሃነ ለትግራይ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ከሶስት አመት በፊት በኤች አይቪ ስርጭት እና መቆጣጠር የተሻለ ጤና  አፈፃፀም ነበረው ብለዋል።

አሁን ላይ ግን  የኤችአይቪ ስርጭቱ ወደ ከፋ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። በፀጥታ እጦት ወቅት በርካታ ሴቶች እና እናቶች የመደፈር አደጋ ተጋላጭ በመሆናቸው  እንዲሁም መድኃኒት ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎችም በመድሀኒት እጥረት በማቋረጣቸው  ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የክልሉ ጤና ቢሮ ባደረገው ጥናት 5 በመቶ የኤች አይቪ ስርጭት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በክልሉ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ስርጭቱ ተስፋፍቷል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ26ሺ በላይ ሰዎች ምርመራ አድርገው ከ500 በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል፡፡

እንደ ክልል ከህፃናት የተጓዳኝ በሽታዎች መድኃኒት እጥረት እንዲሁም ከመመርመሪያ ኪት ውጪ የተሻለ የመድኃኒት አቅርቦት አለ ብለዋል፡፡

የህጻናት መድሀኒት እና የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪት እጥረት መኖሩ ግን መስራት ከምንፈልገው በታች እንድንሰራ አድርጎናል ሲሉ አቶ ፍሥሀ ብርሃነ ተናግረዋል፡፡

ሁሉንም ነዋሪ መርምሮ የስርጭት መጠኑን ለማወቅ አስፈላጊ ቢሆንም  በመመርመሪያ መሳሪያ እጥረት ምክንያት ምርመራውን ማከናወን አልተቻለም።

በሽታው ከአስጊነቱ የተነሳ ያሉበትን የጤና ሁኔታ የማያውቁ ነገር ግን  በትዳር የሚኖሩ እና የተፈናቀሉ ወገኖች  ላይም መስራት እንደሚጠበቅ አስተባባሪዉ ተናግረዋል ።

ትግራይ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል የተባለ ሲሆን ስርጭቱ በ10 ነጥብ 5 በመቶ መጨመሩን ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በክልል በሚገኙ 37 የጤና ተቋማት በተደረገ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ፤ እስከ ጦርነቱ ጅማሮ 1 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው የቫይረሱ ስርጭት አሁን ላይ 10 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷልም ተብሏል፡፡

በጦርነቱ ወቅት በክልሉ ከ120 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ደርሷል ተባለ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አምስት በመቶ በሚሆኑት ላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቶባቸዋል።

“በተለይም ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ላይ ቫይረሱ በከፍተኛ መጠን መገኘቱ ጉዳዩን እጅግ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ያደርገዋል” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

አክለውም፤ በየዕለቱ ከ20 እስከ 25 የሚሆኑ ሰዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ ምርመራ እንደሚያደርጉ እና ከእነዚህም ውስጥ ቢያንስ በኹለት ሰዎች ላይ ቫይረሱ እንደሚገኝባቸው ተግልጿል።

በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ እንደመጣ የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት የገለጸ ሲሆን በ2023 በቫይረሱ የተያዙ ጠቅላላ ዜጎች ቁጥር 603 ሺህ ደርሷል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 10 ሺህ ሰዎች በኤችአይቪ ኤድስ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን 8257 ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በቫይረሱ እንደሚያዙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *