አዲሱ የአውሮፓ ህብረት ሕግ በአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ላይ የሕልውና አደጋ ደቅኗል ተባለ

የአውሮፓ ህብረት ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው አዲስ ህግ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን የሚጎዱ ምርቶችን ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት ገበያዎች እንዳይገቡ እና እንዳይሸጡ አደርጋለሁ ብሏል፡፡

የምድርን ሙቀት ለመከላከል እና የደን ምንጣሮን ለመከላከል ይረዳል በሚል የተዘጋጀው ይህ ህግ ከደን ምርቶች ጋር የተያያዙ ምርቶች በአውሮፓ የገበያ እድል እንዳያገኙ መከልከል እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ማበረታታት የህጉ ዋነኛ ዓላማ ነው፡፡

ይህ ሕግ የጫካ ቡናዎችን ወደ አውሮፓ እና ሌሎች ዓለም ገበያ መዳረሻዎች የምትልከው ኢትዮጵያን እንደሚመለከት ስጋቶች ተነስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ጉዳዩ እንዳሳሰበው ገልጾ አዲሱ የአውሮፓ ህግ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንዲረዳ ካልተደረገ ሚሊዮኖች ወደ ድህነት ሊወርዱ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) ለአልዐይን እንዳሉት “በኢትዮጵያ ቡና የተገኘው በጫካ ውስጥ ነው፣ ቡና ያለ ጫካ ጣእሙ ጥሩ አይሆንም፡፡ ቡናን እና ጫካን መለየት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ቡናን ለማምረት ጫካን መመንጠር አይጠበቅም“ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የደን ጥበቃ ህግ አላት፣ ደን መመንጠር እስከ 15 ዓመት የሚያሳስር ወንጀል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “የኢትዮጵያ ቡና ገበሬዎች ቡናን ከሌላ ተክል ጋር አብረው ነው የሚተክሉት፡፡ አውሮፓ ለኢትዮጵያ የካርበን ክፍያ መክፈል አለባቸው እንጂ እኛን ደን ትመነጥራላችሁ ሊሉን አይገባም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በኢትዮጵያ እንደ ብራዚል ግልጽ የደን ምንጠራ አይደርግም፡፡ በኢትዮጵያ ቡና እና ጫካ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸውም ብለዋል፡፡

ይሁንና በዚህ ህግ ምክንያት እና እኛ አውሮፓዊያንን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታን አስረድተን ማሳመን ካልቻልን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ለጉዳት እንደሚዳረጉም ፕሬስዳንቱ ገልጸዋል፡፡

“የአውሮፓ ቡና ደንበኞቻችንን ማጣት የለብንም፡፡ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ቋሚ የቡና ሸማች ደንበኛ ነው ያላት” የሚሉት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) ቡናችንን በአውሮፓ መሸጥ ካልቻልን ቡና አምራች ገበሬው ቡናን እየነቀለ ሌሎች ምርቶችን ወደ መትከል ሲያመራ በሀገር ላይ ድህነትን ማምጣቱ እንደማይቀርም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ቡና ምርት ውስጥ 30 በመቶው ወደ አውሮፓ እንደሚላክ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በተለይም ጀርመን፣ ስዊድን እና ሌሎችም ሀገራት ዋነኛ ደንበኞቻችን ናቸው ብለዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ፣ እስያ እና ሌሎች ሀገራት የኢትዮያ ቡና የሚላክባቸው ሀገራት ሲሆኑ እነዚህ ደንበኞች በአነስተኛ ዋጋ ብዙ ምርት የሚገዙ እና ቋሚ ያልሆኑ ደንበኞች እንደሆኑም ፕሬዝዳንቱ ተገልጿል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንዲረዳ እንደ ሀገር የተለያዩ የመንግስት እና የንግድ ተቋማት የተሳተፉበት ቡድን ተዋቅሮ ስራ በመሰራት ላይ ነውም ተብሏል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለም ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እና አሳታፊ ያደረገ የደን ፓኬጅ ፕሮግራም ለመስራት እቅድ መውጣቱንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል እና የውጭ ገዢዎቻችንን ለማሳመን የራሳችን እቅድ አለን የሚሉት ሁሴን አምቦ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድበን የቡና አምራች አካባቢዎች በአየር ንብረት ለውጥ እንዳይጎዱ የአካባቢ ትበቃ ስራዎች እየሰራን ነው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2016 ዓም ወደ ውጭ ሀገራት ከተላከ ቡና 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት እቅድ ያላት ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተገኘው ገቢ 570 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ ሲሶው ወይም 33 ሚሊዮን ህዝብ በቡና እና ተያያዥ ስራዎች የሚተዳደር ሲሆን ከ5 ሚሊዮን በላይ ይህሉ ደግሞ የቡና ገበሬዎች ናቸው፡፡

ጀርመን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ዋነኛ የኢትዮጵያ ቡናን የሚገዙ ቀዳሚ አራት ሀገራት ሲሆኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቻይና ከኢትዮጵያ የምትገዛውን ቡና በማሳደግ ላይ ነች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *