ራይላ ኦዲንጋ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት እንደሚወዳደሩ ገለጹ

ኬንያዊው ራይላ ኦዲንጋ የወቅቱ የወቅቱን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማትን ለመተካት በሚደረገው ምርጫ ላይ መወዳደር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ መሃማት የስልጣን ጊዜያቸው የፊታችን ሐምሌ ያበቃል፡፡

ይህን ተከትሎም ሙሳ ፋኪ መሀማትን ለመተካት ሀገራት ከወዲሁ እጩዎቻቸውን እያቀረቡ ሲሆን ኬንያዊው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡

ራይላ ኦዲንጋ ለዚህ እንዲረዳቸው የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ኦሊሶጎኖ ኦባሳንጆ ሀገራትን እንዲያሳምኑለት እንደመረጣቸውም ተናግሯል፡፡

የኬንያ ፕሬዝዳንት ለመሆን አራት ጊዜ ተወዳድረው የተሸነፉት ራይላ ኦዲንጋ በቀጣይ ግንቦት በሚደረገው ምርጫ ለማሸነፍ የተወሰኑ ሀገራትን ለማሳመን ጥረት መጀመራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ይሁንና ራይላ ኦዲንጋ ኬንያን ወክለው ለአፍሪካ ህብረት ለመወዳደር የግድ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ማጽደቅ አለባቸው፡፡

ራይላ ኦዲንጋ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ በ2027 በሚካሄደው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ መወዳደር አለመቻላቸው በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ተብሏል፡፡

የቀድሞው የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አሚና መሀመድ ከአምስት ዓመት በፊት ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ለመሆን እጩ የነበሩ ቢሆንም በሙሳ ፋኪ መሃማት መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ በየ አራት ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን አንድ ተመራጭ ከሁለት ጊዜ በላይ በሊቀመንበርነት ማገልገል እና መወዳደር እንደማይችል የአፍሪካ ህብረት ቻርተር ያስረዳል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በዓመት 184 ሺህ ዶላር ዓመታዊ ደመወዝ ያለው ሲሆን የሊቀመንበር ምርጫው የህብረቱ አባል ሀገራት በሚስጢር በሚሰጡት ድምጽ አሸናፊው ይወሰናል፡፡

የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የሚሳተፉበት 44ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።

37ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ለሚመጡ ታዛቢ ሀገራት ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡

ህብረቱ ባወጣው መግለጫ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተጋበዙ ሀገራት እና ተቋማት ውጪ የሚመጡ ተሳታፊዎችን እንደማያስተናግድ አስጠንቅቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *