የጀርመኑ ናቡ የተሰኘው የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የአፍሪካ ቢሮውን በኢትዮጵያ ከፈተ

ከ125 ዓመት በፊት የተመሰረተው የጀርመኑ የተፈጥሮ እና ብዝሀ ህይወት ጥበቃ ተቋም (ናቡ) የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፍቷል፡፡

የናቡ ፕሬዝዳንት ጆርግ አንድሪያስ ክሩገር እንዳሉት ኢትዮጵያ የብዝሃ ህይወት ሀብት በብዛት ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል አንዷ በመሆኗ እና ከአፍሪካ ጋር ለሚኖረን ግንኙነት መግቢያ በመሆኗ ቢሯቸውን በአዲስ አበባ ለመክፈት እንደወሰኑ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እና ተቋማት ጋር ያለንን ግንኙነት በማቀላጠፍ ተጨማሪ የተፈጥሮ እና ብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራዎችን ለማስራት ቢሯችንን በአዲስ አበባ ለመክፈት አነሳስቶናልም ብለዋል፡፡

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው ይህ የተፈጥሮ እና ብዝሃ ህይወት ጥበቃ ተቋም በአውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ7 ሀገራት ላይ እየሰራ ሲሆን በኢትዮጵያ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ዋጋ ያላቸው ፕሮጀክቶቹን እየተገበረ መሆኑን የናቡ ፕሬዝዳንት በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየሰራባቸው ካሉ ፕሮጀክቶች መካከልም በደቡብ ምዕራብ ክልል ስር ባለው የከፋ ስነ ምህዳር ጥበቃ፣ ሸካ የደን ጥበቃ፣ በኦሮሚያ ክልል ያዩ ስነ ምህዳር ጥበቃ እንዲሁም በአማራ ክልል ጣና ሀይቅ ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ፕሮጀክት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የአፍሪካ ቢሮውን በኢትዮጵያ የከፈተው ይህ ድርጅት በቀጣይ ዓመታት የሚሰራባቸውን የተፈጥሮ እና ብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራዎቹን እያሰፋ እንደሚሄድ የናቡ አፍሪካ ሀላፊ ስቫን ቤንደር ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በተለይም ህብረተሰቡን፣ ባለሀብቶችን እና በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ሀላፊዎችን እና ባለሙያዎችን ባሳተፈ መንገድ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ሀላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ናቡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ጋና፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኡጋንዳ፣ ማዳጋስካር እና ኮቲዲቯር የሚፈጽማቸው የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በፈረንጆቹ 1899 በጀርመን በርሊን የተመሰረተው የተፈጥሮ እና ብዝሀ ህይወት ጥበቃ ተቋም (ናቡ) በአውሮፓ እና ጀርመን እድሜ ጠገብ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን አሁን ላይ 900 ሺህ በጎ ፈቃደኞች አሉት፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *