በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ 018 ቀበሌ ልዩ ስሙ አለኋት ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ነበር ኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ወጣቶች መውጫ ስፍራ በአለት የተደፈነባቸው፡፡
በማህበር ተደራጅተው ኦፓል እንዲያወጡ የተደራጁት እነዚህ ወጣቶች ቁጥራቸው 20 ሲሆን ከመሩት በህይወት ለማትረፍ የአካባቢው ማህበረሰብ ሌት ተቀን በፈረቃ እየቆፈረ መሆኑን የዞኑ መንግስት ኮሙንኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ እያሱ ለአልዐይን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ እያሱ ገለጻ ከሆነ ወጣቶቹ ሌሊት ላይ ማዕድኑን ለማውጣት እየቆፈሩ እያሉ መውጫቸው በዓለት የተዘጋ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ በተመሳሳይ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ጉዳዩን ለህዝብ አሳውቀዋል፡፡
ጥር 30 ቀን የተከሰተው ይህ አደጋ ከመሬት ውስጥ ባለው ዋሻ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች የደላንታ ወረዳ እና የአካባቢው ማህበረሰብ በዘመቻ እየቆፈረ ነው የተባለ ሲሆን ወጣቶቹ ያሉት በግምት 750 ሜትር ርቀት ላይ ይሆናልም ተብሏል፡፡
እስካሁን በተደረገው ጥረትም 50 ሜትር ቁፋሮ እንደተቆፈረ የተናገሩት ሀላፊው ቦታው አለታማ እና የቁፋሮ ማሽን ለማስገባት አመቺ አለመሆኑ ጥሩን ፈታኝ አድርጎታል ሲሉም አክለዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ኦፓል ማዕድን በማውጣት ስራ ላይ የነበሩ ወጣቶች ተማሳሳይ አደጋ አጋጥሟቸው ነበር ያሉት አቶ እያሱ በተደረገው ርብርብ ከ11 ቀናት እልህ አስጨራሽ ቁፋሮ በኋላ ሁሉንም ወጣቶች በህይወት ማግኘት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
አቶ እያሱ አክለውም ወጣቶቹን በህይወት ለማትረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረው በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ሁሉንም ወጣቶች በህይወት ለመታደግ ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ወሎዋ ደላንታ ወረዳ በኦፓል ማዕድን የበለጸገች ሲሆን መንግስት ወጣቶችን በማደራጀት ማዕድኑን እየገዛ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን በመንጌ ወረዳ ሸጎል ቀበሌ አሚር ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ተደርምሶ የስድስት ሰዎች ህይወት እንዳለፈ የወረዳው ፖሊስ አስታውቆ ነበር።
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ማዕድናት በባህላዊ መንገድ እየወጡ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሲሆን አደጋዎች ሲደርሱም ተጎጂዎችን ከሞት ለማትረፍ ጥረት የሚደረገው በሰው ሀይል ብቻ በመሆኑ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በዛው ልክ ከፍተኛ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ኦፓል ማዕድንን ጨምሮ ሌሎች ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 243 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ የነበረ ቢሆንም የተገኘው ገቢ ግን 143 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ገቢው የተገኘው ወርቅ፣ ኦፓል፣ ታንታለም፣ ሊቲየም ኦር፣ ጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሲሆን አውሮፓ እና እስያ ደግሞ ዋነኛ የገበያ መዳረሻዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከማዕድናት የምታገኘው ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ የመጣ ሲሆን ህገወጥ የማዕድናት ግብይት እና የጸጥታ ችግሮች ለገቢው መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ባሳለፍነው ዓመት በጋምቤላ ክልል በህገ ወጥ መንገድ ወርቅን ጨምሮ ማእድን ማውጣት ሰራ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገራት ዜጎች መያዛቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ በክልሉ 3 ኢትዮጵያውያንም ከውጭ ሀገራት ማዕድናት አዘዋዋሪዎች ጋር ተይዘዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 47 የውጭ ዜጎች ወርቅን ጨምሮ በማእድን ማውጣት ስራ ላይ ተሰማርተው ሲያዙ 9 የግል ማህበራትና 7 ኢትዮጵያውያንም በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብላል።