ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ከሆነችው ባህርዳር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው መራዊ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ከሰሞኑ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ ተቀስቅሶ ነበር፡፡
በዚህ ውጊያ ምክንያት የፋኖ ታጣቂዎች የመራዊ ከተማን ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ለቀው መሄዳቸውን ተከትሎ ወደ ከተማው የገባው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ50 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎችን እንደገደሉ ቢቢሲ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ዘግቧል፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት ከሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነዋሪዎቹን ከመንገድ ላይ እና መኖሪያ ቤታቸው በማሰባሰብ ገድለዋቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በኢምባሲው ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ባወጡት መግለጫ በመርዓዊ ከተማ የተፈጸመው የንጹሃን ዜጎች ግድያ እንደሚያሳስባቸው፣ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠይቀዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚረብሹ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ማሲንጋ አለመግባባቱን በጦርነት ሳይሆን በውይይት እንዲፈቱ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎች በተለይም የገጠር አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ሲያዙ ከተሞች ደግሞ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተይዘዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር፡፡
ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን በሁሉም የክልሉ ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ እንደቀጠለ ነው፡፡
አሜሪካም በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ እንዳሳሰባት ያስታወቀች ሲሆን ጉዳዩ በድርድር እና ውይይት እንዲፈታም ጠይቃለች፡፡
በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ አዋጅ ምክንያት በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲን ወክለው የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑት ውስጥ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) እና ክርስቲያን ታደለ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ይታወሳል።
በአጠቃላይ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር በተያያዘ በባህር ዳር ፣ በጎንደር እና በኮምቦልቻ ከተሞች 706 ሰዎች መታሰራውን የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ጌዴዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን እንደማይደግፍ ገልጾ በአማራ ክልል የተጣለው አዋጅ ስድስት ወር ሳይሞላው እንደሚነሳ ከመንግስት ቃል እንደተገባለት መናገሩ ይታወሳል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት እንደሚገድብ እና በክልሉ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስራዎቹን ተዘዋውሮ መስራት እንዳልቻለም ህብረቱ አስታውቋል፡፡