ሱዳን የኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ዶላር የኤሌክትሪክ እዳ እንዳለባት ተገለጸ

ጎረቤት ሀገር ሱዳን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከሚገዙ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ለዓመታት የተጠቀመችበትን እዳ አልከፈለችም ተብሏል፡፡

ሱዳን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተጠቀመችበትን 70 ሚሊዮን ዶላር እዳዋን ባለመክፈሏ ምክንያትም የሚቀርብላት የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን በ50 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡

ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ግብጽ  እና ቻድ ደግሞ ሱዳናዊያን የተጠለሉባቸው ሀገራት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለጎረቤት ሀገራት ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ሽያጭ 66 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 47 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የፌደራል ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።

ሱዳን ባለባት የጸጥታ ችግር ምክንያት ከዚህ በፊት የተጠቀመችበትን የኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ በወቅቱ መክፈል አለመቻሏ ለገቢው መቀነስ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከሚገዙት ሀገራት መካከል ጅቡቲ እና ኬንያ ከዚህ በፊት በሚገዙት ልክ ሀይል እንዳልገዙም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል፡፡

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ለ25 ዓመታት የሚቆይ የኤሌክትሪክ ኃይል የግዥ ስምምነት ያላት ሲሆን አሁን ላይ 200 ሜጋዋት በመውሰድ ላይ ስትሆን በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ ወደ 400 ሜጋዋት ከፍ እንደሚል ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ ለሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በማስጠናት ላይ ስትሆን ለታንዛኒያ ለመሸጥም ውይይቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የሚያገኙ ኢትዮጵያዊያ 52 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ የሀገር ውስጥ ፈላጎት ሳይሟላ ሀይል ለምን ወደ ጎረቤት ሀገራት ይላካል የሚሉ ወቀሳዎች በመንግስት ላይ እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡

መንግስት በበኩሉ የኤሌክትሪክ ሀይል ወደ ውጪ ሀገራት የምሸጠው የሰዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሲቀንስ ሌሊት ላይ ነው እንጂ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በመተው አይደለም፣ የውጭ ምንዛሬም ለማግኘት ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግዙፉን የሀይል ማመንጫ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት ላይ ስትሆን ግብጽ እና ሱዳን ይህ ግድብ የውሃ ፍላጎታችንን ይጎዳል በሚል ተቃውመዋል፡፡

ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታው 94 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

ኢትዮጵያዊያን በሚያዋጡት ገንዘብ እና በመንግስት ወጪ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ በ5ሺህ 200 ሜጋ ዋት ሀይል በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ነው።

የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 350 ሜጋ ዋት ሀይል ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሀይል በማመንጨት ላይ ይገኛል።

ግድቡ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *