ብሪታንያ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለማቅረብ የ125 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገች

የብሪታንያ የአፍሪካ ልማት ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላ ድጋፉን አድርገዋል ተብሏል።

ሚንስትሩ ከጉብኝታቸው በኋላ እንዳሉት አሳሳቢ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር በቀጣይ ወራት 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ይደርሳክ ብለዋል።

የ125 ሚሊየን ዶላር ድጋፉ ለሶስት ሚሊየን ሰዎች ህይወት አድን እርዳታ ለማቅረብ እንደሚውልም ተገልጿል።

አስቸኳይ ድጋፉ በአልሚ ምግብና ሌሎች ወሳኝ ግብአቶች ምክንያት እየተከሰተ የሚገኘውን ሞት ለመቀነስ ለ75 የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን ለማቅረብ ነውም ተብሏል።

የአውሮፓ ህብረት ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ በድርቅ እና ግጭቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያቶች ለእርዳታ የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ በመምጣት ላይ ይገኛል።

የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን እንዲሁም 21 ህጻናት ደግሞ ህይወታቸው አልፎ መወለዳቸውን አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ አደጋ እና ሥራ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ብቻ 4 ሚልየን የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቁን ይታወሳል።

እንደ ሂዩማን ራይትስ ዋች ገለጻ አሁንም በትግራይ፣ በአፋር እና አማራ ክልል የምግብ ዋስትና እጦት እንደቀጠለ ነው ያለ ሲሆን በመንግስት ሃይሎችና ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭት ነገሮችን እያባባሰ ነው ሲል ገልጿል።

በትላንትናው ዕለት በአማራ እና ትግራይ ድርቅ እና ረሃብ ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) “ለችግሩ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱና አሁንም ድረስ በክልሉ የቀጠለ ግጭት በመኖሩ ምክንያት” ረሀቡ እንደቀጠለ የሚገኝ ሲሆን በእዚህ ረሀብ ምክንያት በርካታ ሰዎች እና እንስሳት እየሞቱ ይገኛሉ ብላል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች የዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አክመድ የሰጠውን ሽልማት ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

የዓለም መሪዎች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ መገንዘብ አለባቸው በሚል ጥሪውን ያቀረበው ሂዩማን ራይትስ ዋች በርካታ ኢትዮጵያዊያን በረሀብ እየሞቱ ጠቅላይ ሚንስትሩን መሸለም ስህተት ነው ሲል ፋኦን ወቅሷል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *