ኢትዮጵያ ከቆዳ እና ማዕድናት ንግድ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷ ተገለጸ

በ2016 በጀት ዓመት ሥድስት ወራት 100 ሚሊየን ዶላር ማጣቱን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ፀሐፊ እንዳለ ሰይፉ፥ ባለፉት ሥድስት ወራት 124 ሚሊየን ዶላር ከቆዳ ምርቶች ሽያጭ ለማግኘት ታቅዶ መሰራቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ማሳካት የተቻለው 14 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ብቻ መሆኑን ተናግረው በግማሽ ዓመቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

የቆዳ ዘርፉ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ የገቢ ማሽቆልቆል እንዳጋጠመውም አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የሥራ ማስኬጃ በጀት እጦትና ለዘርፉ የተሰጠው የትኩረት ማነስ ለገቢው መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያትም የቆዳ ፋብሪካዎች ከሥራ ውጭ እየሆኑ እንደሚገኙም ማህበሩ አስታውቋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ ከጥሬ ቆዳና ሌጦ ወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 57 ሺህ 142 የከብት ቆዳን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 400 ሺህ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ  38 ሺህ 122 የዳልጋ ከብት ጥሬ ቆዳን ወደ ናይጄሪያና ቶጎ መዳረሻ አገራት በመላክ 203ሺህ ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብሏል፡፡

ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ ጋር ሲታይ የ50.7 በመቶ ሲሆን በኢትዮጵያ-ኬንያ ሞያሌ በኩል የጥሬ ቆዳ ኮንትሮባንድ ንግድ መኖሩ እንዲሁም በጥሬ ቆዳ ወጪ ንግድ ላይ 150 በመቶ ቀረጥ መኖሩ የእቅዱ እንዳይሳካ ማድረጉንም ሚኒስትሩ ገልጿል፡፡

እንዲሁም የማዕድን ወጪ ንግድ ቅናሽ ያሳየ ሌላኛው ዘርፍ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 243 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ገቢ ግን 143 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በስድስት ወሩ ሶስት ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ መመረቱም ተመላክቷል።

ገቢው የተገኘው ወርቅ፣ ታንታለም፣ ሊቲየም ኦር፣ ጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ነው ተብሏል።

በ2016 በጀት ዓመት ስራ ላይ ያሉት 11 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ ፋብሪካዎች በዓመት 14 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንዳላቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ሲሚንቶ ፍላጎት 36 ሚሊየን ቶን ሲሆን  ባለፉት ስድስት ወራት የተመረተው ሲሚንቶ ግን ሶስት ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ብቻ ነው ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት ያሽቆለቆለ ሲሆን በኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች ያለው አለመረጋጋት ለትራንስፖርት ምቹ ሁኔታ በመጥፋቱ የሲሚንቶ ምርት እንዲስተጓጎል አድርጓል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *