የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፎልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት ሰራዊቱ “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ጥቃት” ለመመከት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ዋና አዛዡ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ለ24ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መኮንኖች ባስመረቀበት ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅት “በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ጥረት እያደረገች ያለችበት ነው” ያሉት አዛዡ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች የውስጥ ችግሮችን ለማባባስ “የቋመጡበት እና የቆረጡበት” ወቅት እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ “ከቀይ ባህር ተገፍታ በመቆየቷ የደረሰባትን የኢኮኖሚና የጸጥታ ተግዳሮቶችን እና ስብራቶችን” ለመቅረፍ “እየሞከረች” ያለችበት መሆኑን ልብ ሊሉት እንደሚገባ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ለተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖቹ አሳስበዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የኢትዮጵያን ዕድገት “በበጎ የማይመለከቱ” እና “ታሪካዊ ጠላቶቻችን” ሲሉ የጠሯቸውን ኃይሎች በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት ወደብ አልባ ሀገር መሆኗን ተከትሎ የባህር ሀይሏን በይፋ ያፈረሰች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የባህር ሀይሏን ዳግም በማደራጀት ላይ ትገኛለች፡፡
ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የባህር ሀይሏን ዳግም ለማጠናከር የጀመረችውን ጥረት ለማገዝ ስምምነት ያደረገች ሲሆን የባህር ሀይሎችን እና ሌሎች አጋዥ መሳሪያዎችን ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮም ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ የባህር ላይ ዉጊያዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ መሳሪያዎችን እያደሰች እና ለጦርነት ዝግጁ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ጦርነቱ ቆሟል፡፡
በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎች በተለይም የገጠር አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ሲያዙ ከተሞች ደግሞ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተይዘዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር፡፡
ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን በሁሉም የክልሉ ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ እንደቀጠለ ነው፡፡