የተገኘው በጀት የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪን ምርታማነት ለማሳደግ እና ለማዘመን እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪን ለማልማት የሚያስችል የ28 ሚሊየን ዶላር ሥምምነት ተፈራርመዋል።
ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና የዩኒዶ የኢትዮጵያ ተወካይ ካልባሮ አውሬሊያ ፓትሪዚያ ተፈራርመውታል።
ፕሮጀክቱ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት በኩል የሚተገበር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም የዘርፉን ኢኮኖሚ ለማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ልማትን ለማሳደግ እንዲሁም የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶችን በመቀነስ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመተግበር እንደሚያስችልም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ የነበረች ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ውስጥ በጦርነት ውስጥ መቆየቷ ጎድቷታል፡፡
በተለይም አሜሪካ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ሀገራት ከሰጠችው ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ገበያዎች እንዲያስገቡ የሚፈቅደው ወይም አግዋ እድልን ማገዷ ከጉዳቶቹ መካከል ዋነኛው ነው፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን በአሜሪካ አዲስ እርምጃ ዙሪያ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን የአግዋ እገዳ እንዲነሳ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኗን ከዚህ በፊት በተሰጡ መግለጫዎች ላይ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ምርቶቿን ከቀረጽ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ከተሞች በመላክ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት ላይ ነበረች።
የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ገብተው በማምረት እና ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያዎች በመሸጥ ላይ የነበሩ ኩባንያዎችን ጎድቷል።
የአሜሪካን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ተከትሎ በርካታ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ለቀው በመሰደድ ላይ ናቸው፡፡
እገዳው ይነሳል በሚል በኢትዮጵያ የቆዩ ኩባንያዎች እስካሁን ሲጠባበቁ የቆዩ ሲሆን ፕሬዝዳንት ባይደን ያራዘሙት ማዕቀብ ተጨማሪ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ እንዲሰደዱ ሊያደርግ እንደሚችል ተሰግቷል።