የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጉዳይ ሊሰበሰብ ነው

የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጉዳይ ላይ ሊሰበሰብ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በዚሁ መሰረት ሶማሊያ ባለፈው ሳምንት  ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የተመድን ቻርተር ጥሷል በሚል ምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲቀመጥ እና እንዲወያይበት አመልክታም ነበር።

ይህንን ተከትሎም የጸጥታው ምክር ቤት የወሩ ፕሬዝዳንት ፈረንሳይ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት አጀንዳ ስር ለመምከር ስብሰባ መጥራቷ ታውቋል።

የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ባለው ችግር ዙሪያ በዝግ እንደሚመክር ተመድ ገልጿል።

የተባሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሀና ስርዌ ቴተ በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባው ላይ ቀርበው በበኢትዮጵያና ሰማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል።

የጥር ወር የጸጥታው ምር ቤት ፕሬዝዳንት ፈረንሳይ ስብሰባውን የጠራችው ሶማሊያ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል በተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ በስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ በሰጡት ማብራሪያ፤  “የቀይ ባህርን የመጠቀም ጥያቄያችን ህጋዊ መሆኑን ለዓለም አሳይተናል፤ የእኛ ፍላጎት ቀይ ባህርን መጠቀም ብቻ ነው” ሲሉም አብራርተዋል።

 “በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግስታት መካከል ችግር ይፈጠራል ብዬ ስለማላስብ፤ በህዝቦች መካከል ጥላቻና ቁርሾ እንዳይፈጠር በሰለጠነ እና በተረጋጋ መንገድ መምራት ይፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ከሰሞኑ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት ብትሆን ሶማሊያ እንደማትቃወም ነገር ግን የሉዓላዊ ሀገርን ግዛት በመያዝ ግን ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ጉዳዩን ሁላችንንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መፍታት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ”ም ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ወደብ ቢኖራት ተቃውሞ የለንም፣ ለድርድርም ዝግጁ ነን ነገር ግን የሌላ ሀገር ግዛትን በመውሰድ ግን ሊሆን አይገባም” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት ስምምነት የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት የማይጥስ መሆኑን ኢትዮጵያም በርበራ ወደብ ላይ ብቻ የንግድ እንቅስቃሴዋን እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባህር ሀይሏን መገንባት የሚያስችል ስምምነት እንዳላት በምትኩ ኢትዮጵያ የሀገርነት እውቅና እንደምትሰጥም ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ይፋ አድርገዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *