አንድ ሺህ ጥንድ ተጋቢ ሙሽሮች በአንድ ቀን በአንድ ቦታ ሊሞሸሩ ነው

ያሜንት ኢቬንትስ ጥንዶችን ለመሞሸር የያዘውን ፕሮጀከት አላማ ለማሳወቅ እና ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቀጣይ አብሮ በትብብር ለመስራት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ያሜንት ኢቭንትስ በዚህ ጊዜ እንዳለው “ቤተሰብን መመስረት ሀገርን መገንባት ነው” በሚል መርህ ጥር 5  ቀን 2016  ዓ.ም አንድ ሺህ ጥንድ ተጋቢዎችን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ጋብቻ እንዲመሰርቱ የሰርግ ሁነት አዘጋጅቷል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና በያሜንት ኢቬንትስ መካከል ዛሬ የተፈረመው የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሰነድ የየሺህ ጋብቻ እንደ ሀገር አቀፍ የቤተሰብ ፕሮጀክት እንዲዘልቅ በማድረግ ከቤተሰብ አመሰራረት ጋር የሚገጥሙ ችግሮችን ለማቃለል አላማው ያደረገ ነው፡፡

እንዲሁም ይህ የጋራ ጋብቻ ሁነት አመታዊ ካርኒቫል የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና መተማመንን ከማጠናከር ባሻገር ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ጎብኚዎችን እንዲስብ ለማድረግ መታሰቡም ተገልጿል፡፡

አንድ ሺህ ጥንዶች በአንድ ጊዜ የሚጋቡበት ይህ ዝግጅት 250 ሺህ ሰዎች እንደሚገኙበትም ተገልጿል፡፡

በአንድ ጊዜ ብዙ ጋብቻዎች የተጋቡበት በሚል የአለም ክብረ ወሰን ለመስበር እቅድ ተያዟል የተባለ ሲሆን ጋብቻው የፊታችን ጥር 5 ቀን 2016 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡

በዚህ የጋብቻ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ አልባሳት፣ አመጋገብ እና ቡና አፈላል ባህል ይቀርባል የተባለ ሲሆን በየዓመቱ በተከታታይ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

ይህ የጋራ ጋብቻ በዓል እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ጥምቀት እና መስቀል በዓል በየዓመቱ በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ከሌሎእ የዓለማችን ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎችን የመሳብ እቅድ ይዟል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ በ200 ሺህ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከ16 ዓመታት በፊት በሚሊኚየም አዳራሽ አንድ ሺህ ሙሽሮች በአንድ ቀን በአንድ ቦታ የተጋቡ ቢሆንም ይህ ሁነት ለዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ የትዳር መፍረስ እየተጨመረ የመጣ ሲሆን ባሳለፍነው ዓመት በ2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ብቻ ከ4 ሺህ በላይ ትዳር መፍረሱ ተገልጿል

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ በዚሁ ዓመት 39 ሺህ ሰዎች ትዳር እንደመሰረቱ የከተማ አስተዳድሩ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የፈረሰው ትዳር ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ60 በመቶ ጨምሯል የተባለ ሲሆን የኑሮ ውድነት፣ ግጭትን በውይይት የመፍታት ባህል መቀነስ እና ሌሎችም ምክንያቶች ለትዳር መፍረስ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *