ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞ ቲኬት በብድር መሸጥ ጀመሩ

ዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ክፍያውን ቆይተው የሚከፍሉበትን አዲስ የክፍያ አማራጭ በጋራ አስተዋውቀዋል።

አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን የዳሽን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን “ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል” በሚል የተሰየመው ይህ አገልግሎት በደንበኞች ምርጫ መሰረት በ6 ወር ወይም በ12 ወር የብድር ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሸን ባንክ የሂሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚገባቸው እና በተጨማሪም በባንኩ ቢያንስ ለሶስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል። 

አቶ ዮሃንስ አክለውም አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በሚያመሩበት ወቅት አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላት የሚገባቸው ሲሆን ማስያዣም ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል።

ስምምነቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው  “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ተኮር አሰራርን እንደመከተሉ የተለያዩ ዘመናዊ እና ለመጠቀም ቀላል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል።

የምናበለጽጋቸው ቴክኖሎጂዎች ለደንበኞቻችን ምቹ መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆኖ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጋርም የተጣጣሙ እንዲሆኑ እናደርጋለን። ዛሬም አጋራችን ከሆነው የዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር ለደንበኞቻችን ያቀረብነው አዲስ የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያችን ከአዲሱ የክፍያ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ እንዲሆን አድርገናል።

በዚሁም መሰረት ደንበኞች ስለክፍያ ሳይጨነቁ ጉዟቸውን ማቀድ የሚጀምሩበትን ‘Fly Now Pay Later’ ተብሎ የተሰየመውን የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ ማድረጋችንን ስንገልጽ በደስታ ነው። ይህ የድህረ-ጉዞ ክፍያ አማራጭ ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን ከአየር መንገዳችን እና ከዳሽን ባንክ በኩል ለተሳተፉ አካላት ያለኝን ምስጋና በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

አዲሱን አገልግሎት ለመጠቀም አንድ ደንበኛ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ካሟላ በኋላ በቅርንጫፉ የተፈቀደለትን የብድር መጠን የሚወስድ ሲሆን የተፈቀደለትን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያስችል የአንድ ጊዜ መለያ ቁጥር መልዕክትም በተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚደርሰው ይሆናል።

በመቀጠልም ደንበኛው የተሰጠውን መለያ ቁጥር በአየር መንገዱ የሞባይል መተግበሪያ ላይ በማስገባት ትኬት መቁረጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።

ደንበኞች የተፈቀደላቸው የብድር መጠን ሲያልቅ ማደስ የሚችሉ ሲሆን በአንዴ የወሰዱትን ብድርም ለተለያዩ በረራዎች ከፍለው መጠቀም ይችላሉ።

አገልግሎቱ በተለይም በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ፣ ጅምላ አስመጪዎች እና ለዕረፍት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ውጭ ለሚሄዱ ደንበኞች አመቺ ነው።

በሁለቱ ተቋማት ስምምነት በቀረበው በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈቀደው የብድር ገንዘብ መጠን እስከ ስድስት መቶ ሺህ (600,000) ብር የሚደርስ ነው።

የሚፈቀደው ብድር ወለድ የሚታሰብበት ሲሆን ይህም ደንበኛው በመረጠውና ብድሩን በወሰደበት የጊዜ ገደብ ከብድሩ ጋር አብሮ የሚከፈል ነው።

ብሔራዊ አየር መንገዱ እና ዳሽን ባንክ ወደፊትም የደንበኞችን አገልግሎት ለማዘመን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም በትብብር መስራታቸውን ይቀጥላሉ።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *