ኢትዮጵያ 6 ሚሊዮን ዶላር በስህተት ለሌላ ወገን መክፈሏ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ልማት ባንክ ዓመታዊ መዋጮ መከፈል የነበረበትን ስድስት ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በስህተት ወደ ሌላ አካውንት መላኳ ተገልጿል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ያሉ ሁለት የባንኩ ሰራተኞች በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች ድብደባ፣ እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር።

ባንኩ እንዳለው ሁለት ሰራተኞቹ የቬና የዲልሎማሲ ጥበቃ ስምምነትን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሮ አስተናጋጅ ሀገራት ስምምነትን የጣሰ ክስተት በኢትዮጵያ መፈጸሙንም ገልጿል።

የተፈጠረውን ክስተት ለኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ማመልከቱን የሚገልጸው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጉዳዩ መፈጸም እንደሌለበት፣ ህግ መጣሱን እና ጉዳዩ ተመርምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ በኢትዮጵያ በኩል ቃል ተገብቶልኛል ሲልም በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡

ባንኩ አሁን ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል በገባው መሰረት በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዳልወሰደ እና ጉዳዩ ስለመመርመሩ መረጃ እንዳልሰጠው ገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎም ባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮውን ሊዘጋ እና ሰራተኞቹንም ወደ ሌላ ሀገራት እንደሚያዘዋውር አስታወቆም ነበር፡፡

አሁን ደግሞ የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ያሉ ሰራተኞቹ ባሳለፍነው ወር በጸጥታ ሀይሎች ሃላፊ አብዱል ካማራ ላይ በምሽት ከቢሯቸው ውጭ አካላዊ ድብደባና እስር የፈጸሙት የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚንስትር ጠባቂዎች መኾናቸውን ሰምቻለሁ ሲል ደይሊ ኔሽን ዘግቧል።

ባንኩ በአዲስ አበባ ከነበሩ ሰራተኞቹ መካከልም የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸውን ሰራተኞች ወደ ሌላ ሀገር ማዛወሩን አስታውቋል፡፡

የባንኩ ሰራተኞች በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች የተደበደቡት እና የታሰሩት መንግሥት ለባንኩ መክፈል ያለበት 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ መዋጮ ለባንኩ እንዳልተከፈለ በማሳወቃቸው ነው ተብሏል፡፡

ሌላኛው ታስረው የተደበደቡት፣ የባንኩ የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሃላፊ ቦስኮ ቡከንያ ሲሆኑ የገንዘብ ሚንስቴር ገንዘቡን የላከው አቢጃን ለሚገኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ አካውንት ሳይኾን፣ በባንኩ ኢሜል ስም በተላከለት ሌላ ሜክሲኮ ወይም ፓናማ ለሚገኝ የባንክ ሒሳብ 6 ሚሊዮን ዶላር ስለመክፈሉና መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ምርመራ ስለመጀመሩ መስማቱን ዘገባው ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሃላፊ ቦስኮ ቡከንያ ወደ ቤታቸው ተወስደው ቤታቸው በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች እንደተፈተሸና ላፕቶፖችና ደረሰኞች እንደተወሰዱባቸው ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በስህተት ወደ ሌላ አካውንት ተላከ ስለተባለው ገንዘብ እስካሁን ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ከአንድ ወር በፊት በሰጡት ምላሽ “ከአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ቢሮ ጋር የተፈጠረው ክስተት ባንኩ ቢሮውን እንዲዘጋ አላደረገውም፣ የሁለቱ ግንኙነትም አልተቋረጠም” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ይሁንና የኢትዮጵያ ጸጥታ ሀይሎች በአፍሪካ ልማት ባንክ የአዲስ አበባ ቢሮ ሰራተኞች ላይ ለምን ድብደባ እንደፈጸሙ ከሁለቱም ወገኖች በኩል በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

የአፍሪካ ልማት ባንክ በፈረንጆቹ 1963 በሱዳን ካርቱም በተካሄደ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋሙ እንዲመሰረት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተቋቋመ አፍሪካዊ ተቋም ነው።

ባንኩ በአዲስ አበባ ያለውን የኢትዮጵያ ቅርንጫፉን በ1967 የከፈተ ሲሆን ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የመሰረተ ልማት፣ ግብርና እና ሌሎች የልማት ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *