የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ አዲሱን 5 ቢሊየን ዶላር ሚያወጣ ‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተማ’ ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡
አየር መንገዱ “ኤርፖርት ሲቲ” ብሎ የሚጠራውን ግንባታ ለመጀመር ከጫፍ የደረሰው እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማርካት መሆኑን የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ለማ ያደቻ ተናግረዋል፡፡
የ ‘ዓየር መንገድ ከተማው’ ካልተገነባ ዓየር መንገዱ በዘርፉ እያስመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገት አንጻር እንደሚፈተን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፕሮጀክቱ መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 5 ቢሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፥ በዓመት 100 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አሁን ላይ ዓየር መንገዱ በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ጥቂት ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ የመጀመሪያውን የ ‘ዓየር መንገድ ከተማ’ ግንባታ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ሆቴሎች ፣አፓርትመንቶች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
የአዋጭነት ጥናቱን በማጠናቀቅም ለዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ሳምንት ከቦይንግ እና ኤርባስ የአቪዬሽን ተቋማት 78 አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማቱ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈረንጆቹ 2035 ላይ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር 271 የማድረስ እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቱርክ የኢኮኖሚ መዲና ኢስታምቡል በተካሄደው የዓለም አቪዬሽን ጉባኤ ላይ በተሳተፉበት ወቅት እንዳሉት አየር መንገዱ አሁን ላይ 140 አውሮፕሎኖች እንዳሉት ገልጸው ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን የማስፋት እቅድ እንዳለው ገልጸዋል።
አየር መንገዱ የ2035 እቅዱን ለማሳካትም ተጨማሪ 130 አውሮፕላኖችን መግዛት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በዚህ ዓመት 29 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ያዘዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 17ቱ 737 ማክስ አውሮፕላን፣ አምስት 777 ማክስ አውሮፕላን፣ አንድ 787- እና ስድስት ኤ350-1000 ኤርባስ ከታዘዙት አውሮፕላኖች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
አየር መንገዱ በዚህ በፊት ካዘዛቸው አውሮፕላኖች መካከልም 12ቱን እንደተረከበ የተገለጸ ሲሆን በኮሮና ቫይረስ ተቀዛቅዞ የቆየውን ዓለም አቀፍ በረራ በሙሉ አቅሙ እየተጠቀመ ነው ተብሏል።