ኤምፔሳ ሳፋሪኮም አዲስ ተጠቃሚ እና ግብይታቸውን በM-PESA የሚያካሒዱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን፣ ወኪሎችን እና ነጋዴዎችን የሚሸልምበት ከታህሳስ 1 ቀን እስከ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የ9ዐ ቀናት የሽልማት መርኃ ግብር ትናንት ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ አስጀምሯል።
ተረክ በኤምፔሳ ደንበኞች እና ድርጅቶች የኤምፔሳ አዲስ ተጠቃሚ በመሆናቸው እና ግብይታቸውን በኤምፔሳ በማካሔዳቸው የእጣ ቁጥሮችን በመሸለም ስለ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቱ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር እና አጠቃቀሙን ለማጎልበት ያለመ መርኃ ግብር ነው።
በእጣዎቹ የሚገኙ ሽልማቶች አራት መኪኖች፣ 12 ባጃጆች፣ 2160 የስልክ ቀፎዎች እና የአየር ሰዓት ስጦታዎች ይሆናሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ደንበኞች በአንድ ቀን የሚደርሳቸው ከፍተኛ የእጣ ብዛት 10 ሲሆን ይህም በየእለቱ፣ በሁለት ሳምንት አንዴ እና በወር አንዴ የሚወጡ ሽልማቶችን በሚያስገኘው እጣ አወጣጥ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላችዋል ተብሏል።
ደንበኞች፣ ወኪሎች እና ነጋዴዎች በኤምፔሳ ለሚያደርጉት ለእያንዳንዱ የ20 ብር ግብይት አንድ እጣ በአር የስልክ መልእክት ይላክላቸዋል፡፡ ደንበኞች ኤምፔሳን መጠቀም በመጀመራቸው አምስት እጣዎችን ያገኛሉ።
ተጠቃሚዎች በ20 ብር ብዜቶች እጣ ያገኛሉ የተባለ ሲሆን ከ20 ብር በታች ያሉ ግብይቶች ምንም አይነት እጣ እያስገኙም።
የሎተሪ እጣ አሸናፊ ደንበኞች ከብሔራዊ ሎተሪ ባልሥልጣን ጋር በመተባበር በሁለት ሳምንቱ የሚለዩ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ኤምፔሳ ሳፋሪኮም አሸናፊዎችን በ+251-700 700 700 ብቻ በመደወል እንዴት ሽልማታቸውን መውሰድ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
ሽልማቶቹ አሸናፊዎች በሚኖሩበት ከተማ በሚገኙ የሳፋሪኮም ሱቆች ለአሸናፊዎች ይበረከታሉ የተባለ ሲሆን ደንበኞች የአየር ሰዓት ሽልማት ሲደርሳቸው ከተረክ በኤምፔሳ አጭር የጽሁፍ መልእክት ይደርሳቸውና ወዲያው የአየር ሰዓታቸው ወደ ሳፋሪኮም ስልክ ቁጥራቸው እንደሚሞላላቸው ገልጿል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የገባው ሳፋሪኮም ከትግራይ ክልል ውጪ በመላው አገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎቱን ለደንበኞቹ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት የቴሌኮም አገልገሎቱን ማቅረብ ያልቻለው ይህ ኩባንያ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ አገልግሎት እጀምራለሁ ብሏል፡፡