ኢትዮጵያ ብድራቸዉን መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ተርታ ተመደበች

መንግስት ከወሰደዉ የረጅም ጊዜ ብድር እና ወለድ አከፋፈል ዙሪያ ከአበዳሪዎች ጋር በዚህ ሳምንት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ማቀዱ ተገልጿል

የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ በ2014 በዩሮ ቦንድ ከተበደረዉ የ1 ቢሊዮን ዩሮ እና ወለዱን 33 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ የመክፈል አቅም ስለመኖሩ አበዳሪዎች ከጥርጣሬ ዉስጥ መገባታቸዉን ብሉምበርግ አስነብቧል።

በዘገባዉ ኢትዮጵያ ዛምቢያንና ጋናን በመከተል በአፍሪካ የከሰሩ ሀገራት ተርታን ልትቀላቀል ከጫፍ የደረሰች መሆኑን ዘገባዉ ጠቅሷል።

በተያዘዉ ሳምንት ሐሙስ መንግስት ከአበዳሪ አካላት ጋር ዉይይት የማድረግ እቅድ ስለመኖሩ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

መንግስት ከአንዳንድ አበዳሪ አካላት ጋር ባሳለፍነዉ ሳምንት የተገደበ ዉይይት አድርጎ አበዳሪዎች ኢትዮጵያ ያለባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር የወለድ እዳ የመክፈል አቅም እንደሌላት ተገንዝበዋል ብሏል።

ለዚህም ኢትዮጵያ የዉጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ እጥረት ያለባት በመሆኑ ነዉ ተብሏል። መንግስት የተባለዉን እዳ በገደቡ መሰረት ለመክፈል 14 ቀናት ብቻ ያለዉ መሆኑ በዘገባዉ የተጠቀሰ ሲሆን የብድር መክፈያ ወቅቱ እንዲራዘም የገንዘብ ሚኒስቴር ጥረት እያደረገ ነዉም ተብሏል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ባላት ደረጃም ብድራቸዉን መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ተርታ የተመደበች ሲሆን ይህም በቀጣይ በአበዳሪዎች አመኔታን የማታገኝ ሀገር ሊያደርጋት እንደሚችል ተነግሯል።

ፊች ሬቲንግ የተሰኘዉም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም ኢትዮጵያን ብድራቸዉን መክፈል ከማይችሉ ሀገራት መካከል አንዷ አድርጎ መድቧታል።

29 ብሊዮን ዶላር የውጭ እዳ ያለባት ኢትዮጵያ 50 በመቶ ያለባት ብድር ከቻይና የተበደረችው ሲሆን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲሻጋሸግላት አበዳሪዎቿን ጠይቃለች፡፡

ቻይና ኢትዮጵያ ያለባትን ብድር መክፈያ ጊዜ ለሁለት ዓመት ያራዘመች ሲሆን ዓለም ባንክ እና ሌሎች አበዳሪ ሀገራት እና ተቋማት ተመሳሳይ የብድር መክፈያን እንዲያዝሙላት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗ ን የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጦርነት፣ በኮሮና ቫይረስ እና በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እየተፈተነ ሲሆን ኢኮኖሚዋን ከከፋ ጉዳት ለመጠበቅ ተጨማሪ ብድር ለማግኘት ዓለም ባንክን ጠይቃለች፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ማድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህ ጦርነት ለዓመታት በብድር እና በህዝብ ገንዘብ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን እንዲወድም ያደረገ ሲሆን በአጠቃላይ የ28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በሀገር ላይ እንዳደረሰ ተገልጿል።

የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ የ10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ጥያቄ እንደቀረበለት ገልጾ ብድሩን ለመፍቀድ ተከታታይ ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ባጋጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በርካታ ተቋማት የምርት ግብዓት ከውጭ ሀገራት ለማምታት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደገጠማቸው እና ማምረት እንዳቆሙ የገለጹ ሲሆን ሰራተኞቻቸውን በመበተን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *