የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሄንሪ ኪሲንገር በመቶ አመታቸው አረፉ
ታዋቂው ዲፕሎማት እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የውጭ ፖሊሲ አሳቢ በኮነቲከት በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ትናንት ለሊት መሞታቸውን የአማካሪ ድርጅታቸው ኪሲንገር አሶሺየትስ በመግለጫው ገልጿል።
በፈረንጆቹ በ1969 የፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ከመሆናቸው በፊት በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተው አለም አቀፍ ግንኙነቶችን አስተምረዋል።
የፕሬዚዳንት ጄራልድ ፎርድ የመንግስት ፀሀፊም ሆነው አገልግለዋል።
ጎበዝ ተደራዳሪ ተብለው የተወደሱ ሲሆን በ1970ዎቹ አሜሪካ ከሶቪየት ኅብረት ጋር ያለውን ግንኙነት እንድትሻሻል ኪስንገር ትልቅ ሚና ነበራቸው።
አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት የተሻለ ለማድረግ መንገድ ጠርገዋል። እ.ኤ.አ. በ 1973 ኪሲንገር የፓሪስ የሰላም ስምምነትን በማሳካታቸው ከዲፕሎማት ለዱክ ቶ ጋር የኖቤል የሰላም ሽልማትን ተጋርተዋል ።
በፓሪሱ ስምምነት የአሜሪካ ወታደሮች ከቬትናም ወጥተዋል። እ.ኤ.አ. በ1974 የእስራኤልን ከሶሪያ እና ግብፅ በማደራደር የዮም ኪፑር ጦርነትን በይፋ እንዲቆም አርገዋል።
በህይወት ዘመናቸው 19 መፅሀፍትን የጻፉት ኪሲንጀር በጀርመን ከአይሁዳውያን ወላጆቻቸው እንደተወለዱ ይገለጻል፡፡
ሄንዝ አልፈርድ ኪሲንጀር (ሄነሪ ኪሲንጀር) እስራኤል ከአረብ ሀገራት ጋር ግንኙነት እንድትጀምር በማድረግም ስማቸው ይወሳል።
የቬትማኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በ1973 በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት በማርቀቅም የእኝህ ዲፕሎማት ድርሻ ትልቅ ነበር ተብሏል፡፡
ሄነሪ ኪሲንጀር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቅነታቸው በርካቶች ቢያወድሷቸውም በጦር ወንጀለኝነት የሚከሷቸውም ጥቂት አይደሉም።
በተለይ በላቲን አሜሪካ ጸረ ኮሚዩኒስት የሆኑ ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣዎችን መደገፋቸው ያስወቅሳቸው ነበር።
በፈረንጆቹ 1973 የተበረከተላቸው የኖቬል ሽልማትም አወዛጋቢ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ኪሲንጅር በካምቦዲያ የቦምብ ጥቃት እንዲፈጸም ሃሳብ አቅርበው በቬትናም ሰላም ለማስፈን ጥረት አድርገዋል በሚል ሽልማቱ መሰጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ያነሱ ሁለት የኖቬል ሽልማት ኮሚቴ አባላትም ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው አይዘነጋም።