የኢትዮጰያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ እንደገለጸው መነሻውን አራት ኪሎ ያደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለከንቲባ ቢሮ ማስገባቱን ገልጿል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ “ጦርነት ይቁም! ሠላም ይስፈን፣ መከላከያ ሰራዊቱ ባስቸኳይ ወደ ካምፕ ይግባ!” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በሚል የተዘጋጀው ይህ ሰላማዊ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም በሀገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች ደብዳቤውን ጦርነት እንዲቆም፣ መከላከያ ሠራዊቱ ከዘመተባቸው ክልሎች ወጥቶ ወደ ጦር ካምፑ እንዲመለስና ፖለቲካዊ ውይይቶች እንዲከፈቱ በሰልፉ ላይ እንጠይቃለንም ብለዋል፡፡
የኢትዮጰያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ /ኢህአፓ/ እና ሌሎች ዜጎች አስተባባሪነት የተጠራው ይህ ሰላማዊ ሰልፍ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ትብብር እንዲያደርግም ጥያቄ ቀርቦለታል ተብሏል፡፡
የኢህአፓ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም እንደገለፁት ኢህአፓ እና ሌሎች ሁሉን አቀፍ ሀገር ወዳድ አባላት በመሰባሰብ በጋራ በመሆን ሀገርን የማዳን ሰልፍ መጠራቱን ተናግረዋል፡፡
ሰላማዊ ሠልፉ መነሻውን አራት ኪሎ የድላችን ኃውልት አድርጎ በተለያዩ ጎዳናዎችንና አደባባዮችን በማለፍ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ የዕለቱን መልዕክት በማስተላለፍ ይጠናቀቃልም ተብሏል።
በሠላማዊ ሠልፉ ላይም ከ100 ሺህ ሰው በላይ እንደሚጠበቅ የገለፁት አስተባባሪዎቹ፣ ለዚህ የሚሆን የፀጥታና ደህንነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ሠልፉ በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የጦር ሠራዊቱ ከጦርነት አውድ ውጪ የሚፈፅማቸውን ዘመቻዎችን በማቆም ወደ ጦር ሰፈሩ እንደሚለስ የሚጠይቅ መሆኑንም አስተባባሪዎቹ ተናገግረዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን ከጠሩት አስተባባሪዎች መካከልም እንደ የሺዋስ አሰፋ የመሣሠሉ ፖሊቲከኞችና ሌሎችም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የተዘጋጀ ነውም ተብሏል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት የተከሰተው ጦርነት ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡
በዚህ ጦርነት 800 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደተገደሉ ሲገለጽ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ለአካል ጉዳት ዳርጓል፡፡
ይሁንና አሁንም በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ጦርነት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጁ በተጨማሪ ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና በርካታ ሌሎች ሀገራት ይህ ጦርነት እንዲቆም እና ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት በተደጋጋሚ በሚፈጽማቸው የድሮን እና ከባድ መሳሪያዎች ጥቃት ንጹሃን ዜጎች እየተገደሉ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የፋኖ ታጣቂዎች የአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎቸን የተቆጣጠሩ ሲሆን መንግስት ግን የክልሉ ሰላም ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጥቷል ብሏል፡፡
በቅርቤ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉን ከተሞች እና የመንግስት ተቋማትን ለመቆጣጠር አላማ ያደረገ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡