የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እንደገለጸው ኢትዮጵያ 28 የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በግንባታ ላይ ካሉት የመስኖ ግድቦች ውስጥም 13ቱን በተያዘው የ2016 ዓመት በከፊል ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በዚህ ዓመት እንዲጠናቀቁ በሚል እየተገነቡ ላሉ ግድቦችም 8 ነጥብ 03 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተመልክቷል፡፡
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ 28 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በመከናወን ላይ ነው፡፡
13 የመስኖ ፕሮጀክቶች በከፊል ሲጠናቀቁ 2 ሺህ 450 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ እንደሆኑም ሃለፊው ተናግረዋል፡፡
እየተገነቡ ካሉት ግድቦች በተጨማሪም 27 አዲስ የመስኖ ግድቦችን ለመገንባት የጥናትና ዲዛይን ፕሮጀክት እየተከናወነላቸው ነው የተባለ ሲሆን የሰባቱን ግድቦች የአዋጭነት ጥናት በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዷልም ተብሏል፡፡
የአዋጭነት ጥናት እየተሰራላቸው ያሉ የመስኖ ግድቦች በሰባት ክልሎች ላይ የሚገኙና ሲጠናቀቁ 103 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚያስችሉም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ለአብነትም የቆቦ ጊራና የከርሰ ምድር ውሃ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በ138 ሚሊዮን ብር ተጠግኖ አቅሙን የማሳደግ ሂደት ተጀምሯል፡፡
እንዲሁም 31 ጥልቅ ጉድጓዶችን በመጠገን እና የውሃ መሳቢያ ሞተር ተከላ በማከናወን በፊት ይለማ የነበረውን 2 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ወደ 800 የሚሆን ተጨማሪ ሄክታር ማልማት የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጋምቤል ክልል ከ30 ዓመታት በፊት የተሠራው የአልዌሮ የመስኖ ልማት 10 ሺህ ሄክታር ለማልማት የሚያስችል መሆኑን አውስተው፤ የመስኖ ግድቡን መሠረተ ልማት ለመጠገን እንደሚሠራም አመላክተዋል።
በተያያዘም በቆላማና አርብቶ አደር አካባቢዎች በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች 90 የንጹህ መጠጥ ውሃ ቁፋሮ፣20 የአነስተኛ መስኖ፣ ስድስት የመካከለኛ መስኖ የማስፋፊያ ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢዎቹ የሚገነቡ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ግድቦች 830 ሄክታር መሬት ሰብልና የግጦሽ ሣር ለማልማት የሚያስችሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የመስኖ ውሃ መሳቢያ ሞተሮች (ፓምፖች) በ150 ሚሊዮን ብር እንደሚሰራጩም ተናግረዋል፡፡
የሥራ ተቋራጮች የአቅም ውስንነት፣ የሲሚንቶ እጥረት፣ የካሳ ክፍያ እና የጸጥታ ችግሮች ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ዋነኛ እንቅፋቶች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡