ባለስልጣናት ስለ ባህር በር ጉዳይ የሚሰጡት መግለጫ የተጠናና ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንዳለበት ምሁራን አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የባህር በር ዙሪያ የምሁራን ውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
በዚህ የምሁራን መድረክ ላይ ጥናት ያቀረቡና ውይይት ያደረጉ ምሁራን፣ መንግሥት ስለባህር በር የሚሰጣቸው መረጃዎች የጎረቤት አገሮችን የማያሠጉና ጥንቃቄ የተሞላባቸው እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
‹‹ፍትሐዊ የወደብ አጠቃቀም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት›› በሚል ርዕስ በተስተናገደው በዚህ ዓውደ ጥናት ላይ፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ባለቤት መሆን ስለምትችልባቸው አማራጮች ሰፊ ምሁራዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በጥናት መድረኩ ላይ ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን በማስመለስ ታሪካዊ ድል ያስመዘገቡ ያለፈው ትውልድ ምርጥ ተሞክሮ ታሪካዊ ድል እንደነበር ተገልጿል፡፡
በሰላማዊ መንገድ ኤርትራን በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር በማስተሳሰር የባህር በር ጥያቄን የመለሰ ትውልድ ያፈራችው ኢትዮጵያ፣ ይህን ታሪካዊ ስኬት ማስቀጠል የሚችል ተተኪ ትውልድ ማፍራት ባለመቻሏ የባህር በር አልባ ሀገር ሆና ቀርታለችም ተብሏል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን አሁን ላይ የባህር በርና ወደብን በተመለከተ ግብታዊ አስተያየቶች ሲሰጡ እንደሚሰማ ያነሱ አንዳንድ ተወያዮች፣ ይህ ያልተጠናና ጥንቃቄ የጎደለው አካሄድ ሰላም የናፈቃትን ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ግጭት ሊወስዳት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአንድ ወር በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደብ ያስፈልጋታል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በጎረቤት ሀገራት ያልተወደደ ሲሆን በተለይም ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ፈጥነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሶስቱም ሀገራት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተናገሩ ሲሆን ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቢሰሩም የወደብ ጥያቄን ግን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋሚ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሀይል አማራጭን እንደማትጠቀም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ውይይት እና ትብብር የወደብ አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ ከቀይባህር ትብብር መገለል እንደሌለባት ገልጾ በርካታ ሀገራት ከተለያዩ አህጉራት ወደ ቀይባህር እየመጡ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያም ከዚህ ራቂ ማለት ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ 80 በመቶ የወጪ እና ገቢ ንግዷ በጅቡቲ ወደብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ በየ ዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እየከፈለች ሲሆን አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም በመፈለግ ላይ ትገኛለች፡፡
በርበራ ወደብ፣ ፖርት ሱዳን፣ አሰብ እና ላሙ ወደብን ለመጠቀም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነችም በተለያዩ ጊዜያት አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ20 ዓመት በላይ ከቆዩበት የጦርነት ጊዜ በኋላ በ2018 ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ቢስማሙም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ግንኙነታቸው ሊሻሻል አልቻለም፡፡