የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ፕሬዝዳንትና የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ጀነራል አልቡርሃን በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታና በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

ሰባተኛ ወሩን የያዘው የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጦርነት ከ9 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

ከ5 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለው ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲቆም የሚደረገው ጥረትም ቀጥሏል።

ሁለቱ ሃይሎች በሪያድ በተደጋጋሚ ለድርድር ቢቀመጡም እስካሁን ከስምምነት ላይ አልደረሱም።

በአዲስ አበባም በቅርቡ በሱዳን የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ያለመና ከ80 በላይ የሀገሪቱ የፖለቲካና ሲቪል ድርጅቶች የተሳተፉበት ምክክር መደረጉ አይዘነጋም።

በካርቱም የሚገኘው ኤምባሲዋ በአየር የተደበደበባት ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጋር በመተባበር ሁለቱን ተፋላሚ ሃይሎች ለማቀራረብ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

የሱዳን ጦር በሰኔ ወር በአዲስ አበባ በተካሄደውና የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ መሪዎች በተሳተፉበት የአራትዮሽ መድረክ  ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።

ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ በግብጽ እና ሳኡዲ አረቢያ ጉብኝት ያደረጉት የጦሩ አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ጀነራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ በካርቱም ሰላም ለማስፈን ስለሚደረጉ ድርድሮች እና በሱዳን ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሱዳን ጦርነትን ሽሽት ከ100 ሺህ በላይ ሱዳናውያን እና የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በመተማ፣ ጋምቤላ እና ኩምሩክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፤ ከ34 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንንም ከጦርነት ቀጠና ማስወጣት መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ጀነራል አልቡርሃን ከሰሞኑ ወደ ናይሮቢ አቅንተው ከወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር እና ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር የመከሩ ሲሆን በሀገራተቸው ያለውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች ጋር እየተዋጋ ሲሆን የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም፣ ዳርፉር እና በርካታ አካባቢዎች የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች ተቆጣጥረውታል፡፡

በሱዳን ባለው ጦርነት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር 100 ሺህ የደረሰ ሲሆን በመተማ፣ ኩምሩክ እና ጋምቤላ በኩል በርካታ ዜጎች ለደህንነታቸው ሲሉ እየገቡ ይገኛሉ፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *