ኢትዮጵያ ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቂያ ጊዜን አራዘመች

ኢትዮጵያ ETRSS-02 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በወራት ውስጥ እንደምትመጥቅ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም መራዘሙ ተገልጿል፡፡

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሶስት ወራት በፊት በሰጠው መግለጫ በቅርቡ ሶስተኛዋን ሳተላይት አመጥቃለሁ ሲል ገልጾ ነበር፡፡

ይሁንና ETRSS-02 የተሰኘችው ሳተላይት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደምትመጥቅ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በፊት በቻይና አጋዥነት ወደ ሕዋ የመጠቁት ሳተላይቶች የተቀመጠላቸውን የአገልግሎት ጊዜ በመጨረስ ተልዕኳቸውን በስኬት ማጠናቀቃቸውም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ ሶስተኛውን ሳተላይት መምጠቅን በተመለከተ መንግስት የፋይናንስና የኢኮኖሚ አዋጪነት ጥናት ማድረጉን ገልጸዋል።

ጥናቱ ከዚህ በፊት ወደ ሕዋ ከመጠቁት ሳተላይቶች ተሞክሮ በመውሰድ የቀጣዩን ሳተላይት መረጃ ከመጠቀም አልፎ ሌሎች ተልዕኮዎችን በግልጽ ማስቀመጡንም አመልክተዋል።

የሳተላይቱን ጨረታ የተመለከተ መረጃ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ስርዓት ውስጥ እንዲገባ መደረጉንና በቀጣይ ወራት ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚወጣም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ETRSS-02 የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ETRSS-01 የተሰኘች የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።

በታህሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ ET-Smart-RSS የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ ከቻይና ወደ ሕዋ አምጥቃለች።

የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በሕዋ ከሁለት ዓመት ከግማሽ እስከ ሶስት ዓመት እንዲሁም ሁለተኛው ሳተላይት ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ዓመት እንደምትቆይ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በዚሁ መሰረት ሁለቱ ሳተላይቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ የአገልግሎት ጊዜያቸውን አጠናቀው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ለኢዜአ ተናግረዋል።

ETRSS-01 የተሰኘችው ሳተላይት ከተቀመጠላት ጊዜ በላይ ተጨማሪ ዘጠኝ ወራት አገልግሎት መስጠቷን አመልክተዋል።

በቀጣይ ሳተላይቶቹን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የማስወገድ ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።

ከሳተላይቶቹ የተገኙት መረጃዎች ለግብርና፣ ቱሪዝም፣ መሬት አስተዳደር፣ ተፈጥሮ ሀብት፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳና ሌሎች ስራዎች በግብአትነት መዋላቸውን አመልክተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *