በአህያ ደህንነት ዙሪያ የሚሰራው ብሩክ ኢትዮጵያ የተሰኘው የእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅት የአህያ ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን ገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የአህያ ስጋን ወደ ውጪ ሀገራት መላክ የተጀመረ ሲሆን ዓላማውም የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሆነ ይገለጻል፡፡
በዚህ የአህያ እርድ3 እና ንግድ ምክንያት የአህያ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን እና ይህም እንዳሳሰበው ብሩክ ኢትዮጵያ የተሰኘ የአህያ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ አህያ እንዲታረድ እና ስጋና ቆዳው ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ መደረጉ እንደ አገር የአህያ ቁጥር እየተመናመነ እንዲመጣ ማድረጉን የብሩክ ኢትዮጵያ ድርጅት አማካሪ ይልማ አበበ ለመናኃሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
በኢትጵያ የአህያ እርድ በቻይና ባለሃብቶች በመስፋፋቱ ለአገር የውጭ ምንዛሪን ቢያስገኝም፤ እንደ አገር የአህያ መኖር ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም አማካሪው ጠቅሰዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የአህያ እርድ በመካሄዱ የእንስሳቱ ቁጥር ቀንሷል በሚል በብሩክ ኢትዮጵያ የቀረበው ሀሳብ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
በሚኒስቴሩ የስጋ እና ቆዳና ሌጦ ዴስክ ሃላፊ አስመላሽ በርሄ በበኩላቸው፤ “በተደረገ ጥናት እና አሰራር መሰረት ምንም እንኳን የአህያ እርድ ቢከናወንም ቁጥራቸው ሊቀንስ አይችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ለእርድ እንዲቀርቡ የተፈቀደው ያረጁ እና ለማህበረሰቡ አገልግሎት የማይሰጡ አህዮችን ብቻ በመሆኑ ቁጥራቸው ሊቀንስ ይችላል የሚለው ስጋት ሆኖ አይቀርብም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አህያ እንደ አገር የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ በድብቅ እርድ የሚደረግባቸው አካባቢዎች ካሉ ማንኛውም ማህበረሰብ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2015 በጀት ዓመት የአህያ ስጋን ወደ ሆንግኮንግ እና ሌሎች የቻይና ከተሞች በመላክ 3 መቶ ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የእንስሳት ልማት ኢንስትቲዩት አስታውቋል፡፡
በኢንስትቲዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሳህሉ ሙሉ እንደተናገሩት፣ ከአህያ ስጋ ውጪ የአህያ ቆዳን እንደ ቻይና ያሉ ሃገራት ለመድሃኒትነት ስለ ሚፈልጉት የስጋ ምርቱን ወደ ሆንግኮንግ እንዲላክ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ገቢው የተገኘውም በ2015 በጀት አመት 140 ቶን የአህያ ስጋ ምርትን ወደ ውጪ ገበያ በመላክ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በበጀት አመቱ 600 ቶን የአህያ ስጋን ወደ ውጪ ለመላክ አስቀድሞ ታቅዶ እንደነበር ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡
በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከአምናው ተጨማሪ መጠን ያለው የአህያ ስጋ እና ቆዳ ወደ ቻይና እና ሌሎች ሀገራት በመላክ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡