የገንዘብ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር እና የአየርላንድ መንግሥት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
የ8 ሚሊየን 400 ሺሕ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የአየርላንድ የዓለም አቀፍ ልማትና ዳያስፖራ ሚኒስትር ዴዔታ ሾን ፍሌሚንግ ናቸው፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ የመጀመሪያው 5 ሚሊየን ዩሮ ለሴፍቲ ኔት ፕሮግራም እንዲሁም 3 ሚሊየን ዩሮ በጤና ላይ ያተኮሩ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጽልል።
እንዲሁም 400 ሺሕ ዩሮ ደግሞ ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ድጋፍ እንደሚውል በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ከፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ በኋላ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ባደረጉት ንግግር፤ አየር ላንድ ለኢትዮጵያን የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እያደረገችው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ሦስቱም ስምምነቶች በመንግሥት በኩል ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር ተጣጥመው እንደሚተገበሩም ሚንስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
የአየርካንድ ሚኒስትር ዴዔታ ሾን ፍሌሚንግ በበኩላቸው፤ እነዚህ አገራዊ መርሐ- ግብሮች የማህበራዊ ጥበቃ እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው በተለይም ሴቶች እና ሕጻናትን ለመድረስ እንዲተገበሩ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ እና አየርላንድ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ግጭት ውስጥ ገብተው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተበላሽቶም ነበር።
አየርላንድ ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደ የሰላም ስምምነት የተቋጨው ጦርነት አስመልክቶ በተደጋጋሚ በምትሰጠው አስተያየት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ በአየር ላንድ አስተያየት ምክንያት በአዲስ አበባ የነበሩ አራት ዲፕሎማቶች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡም አድርጎ ነበር።
ሁለቱ ሀገራት አሁን ላይ ወደ ቀድሞ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የተመለሱ ሲሆን በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ዉገን ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ በጋር በመስራት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።